በወይዘሪት ዚምባቡዌ ውድድር ነጭ የቆዳ ቀለም ያላት ቆንጆ ማሸነፏ ተቃውሞ አስነሳ
አሸናፊዋ አብዛኛውን የዚምባቡዌ ህዝብ የሚወክል የቆዳ ቀለም የላትም ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው
በሀረሬ ተወልዳ ያደገችው “ወይዘሪት ዚምባቡዌ” በአለም የቁንጅና ውድድር ሀገሯን ወክላ ትሳተፋለች
የ21 አመቷ ብሮክ ጃክሰን በዚምባቡዌ የተካሄደውን የቁንጅና ውድድር አሸንፋለች።
ከ22 አመት በተካሄደው ውድድር ከ10ሩም የዚምባቡዌ ግዛቶችና የሀገሪቱን ዲያስፖራ ማህበረሰብ የወከሉ 25 ቆነጃጅት በተሳተፉበት ውድድር በመዲናዋ ሀረሬ ተወልዳ ያደገችው ብሮክ ማሸነፏ አነጋጋሪ ሆኗል።
አሸናፊዋ በቀጣይ በሚካሄደው የአለም የቁንጅና ውድድር ዚምባቡዌን እንድትወክል መመረጧ ተገቢነት የሌለው ነው የሚሉ ተቃውሞች የተደመጡት ብሮክ የቆዳ ቀለሟ ነጭ በመሆኑ ነው።
አብዛኛውን የዚምባቡዌ ህዝብ የሚወክል የቆዳ ቀለም ሳይኖራት የአፍሪካዊቷን ሀገር ወክላ በአለማቀፍ መድረክ መሳተፍ የለባትም የሚሉ ተቃውሞዎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ብሮክ ያሸነፈችው የተለየ ውበት ስላላት ሳይሆን ነጭ በመሆኗ ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎች የውድድሩ ውጤት እንዲሰረዝ እየጠየቁ ነው።
“አውሮፓዊት እንስት የጥቁሮች የቁንጅና ውድድር አሸነፈች” እስከማለት የደረሰ ተቃውሟቸውን ያሰሙ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ።
“ጥቁር ህዝቦች በራሳቸው የቆዳ ቀለም እንዲኮሩና ራሳቸውን እንዲያከብሩ አሸናፊዋን (ብሮክ) ወደ አለም ቁንጅና ውድድር ባለመላክ አስተማሪ ተግባር መከወን ይገባል” ብሏል አንድ አስተያየት ሰጪ።
ብሮክ ነጭ የቆዳ ቀለም ኖሯት በቁንጅና ውድድር አሸናፊ የሆነች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አይደለችም።
በደቡብ አፍሪካም በዚህ አመት በተደረገ ተመሳሳይ ውድድር ያሸነፈችው ነጭ የቆዳ ቀለም ያላት እንስት ናት።
የዚምባቡዌዋ ብሮክ ጃክሰን ከ25 ተወዳዳሪዎች ብቸኛዋ ነጭ ሆና የማሸነፏ ዜና ግን በርካቶችን ለጥርጣሬ ዳርጓል።
ብሮክ ከዚምባቡዌ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገችው ቆይታ "በቆዳ ቀለም ምክንያት ማንም ተጽዕኖ ሊያደርግብኝ አይገባም፤ ሁላችንም አንድ ነው፤ ሀገሬን በአለማቀፍ መድረክ ወክዬ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እሞክራለው" ብላለች።