የሚስ ዩንቨርስ የቁንጅና ተወዳዳሪዎች እርቃናቸውን እንዲሆኑ መገደዳቸውን ገለጹ
ዳኞች በበኩላቸው ድርጊቱን የፈጸምነው ተወዳዳሪዎች ሰውነታቸው ለውድድር ብቁ መሆኑን ለመገምገም ነው ብለዋል
የቁንጅና ተወዳዳሪዎቹ ጉዳዩን ወደ ህግ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል
በኢንዶኔዢያዋ መዲና ጃካርታ በየዓመቱ የሚካሄደው የሚስ ዩንቨርስ የቁንጅና ውድድር ዘንድሮ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ይገኛሉ።
በዚህ ውድድር ላይ የተለያዩ ሀገራት ቆነጃጅት በመወዳደር አሸናፊ የሆኑት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን አትርፈውበታል።
በየዓመቱ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ዳኞች የተወዳዳሪዎችን ሰውነት ለማየት በሚል ራቁታቸውን እንዲሆኑ እንደተጠየቁ ተወዳዳሪዎቹ ለፖሊስ ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ ያለፉ ቆነጃጅት ወንዶች በተገኙበት ክፍል ውስጥ ልብሳችንን እንድናወልቅ ተደርገናል ይህ ደግሞ መብታችንን መጋፋት ነው ሲሉ ክስ መስርተዋል።
አንድ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ተወዳዳሪ እንዳለችው "መብቴ እንደተገፈፈ ይሰማኛል፣ ይህ ደግሞ በአዕምሮዬ ጤና ላይ እክል ፈጥሮብኛል" ስትል ተናግራለች።
ድርጊቱ ተፈጽሞብናል ያሉ ቆነጃጅት ጠበቃ የሆነችው መሊሳ አንግራኒ እንዳለችው ዳኞች ነን ያሉ የውድድሩ አዘጋጆች ወንዶችም በተገኙበት እና የአዳራሹ በር ባልተዘጋበት ሁኔታ ተወዳዳሪዎች የለበሱትን ልብስ እንዲያወልቁ እና ሰውነታቸውን እንዲያሳዩ ተጠይቀዋል ብለዋል።
ክስ የቀረበለት የጃካርታ ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የውድድሩ አዘጋጆች በበኩላቸው ተወዳዳሪ ቆነጃጅቶቹ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ማድረጉን አምነው ድርጊቱን የፈጸሙት ተወዳዳሪዎቹ ከንቅሳት እና ጠባሳ የጸዳ ሰውነት እንዳለባቸው ለማረጋገጥ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ በፊት በተካሄዱ የሚስ ዩንቨርስ ውድድር ላይ የተሳተፉ ቆነጃጅት በበኩላቸው የተወዳዳሪዎች ሰውነት ለውድድሩ ይመጥናል የሚለውን ማየት የተለመደ ቢሆንም ራቁታቸውን እንዲሆኑ ማድረግ ግን አዲስ ክስተት እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።