ራይሲን ለመተካት በሚደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡት ላርጃኒ ማን ናቸው?
ኢራን በፈረንጆቹ ሰኔ 28 እንዲካሄድ ቀን በተቆረጠለት ምርጫ የሚሳተፉ እጩዎችን መመዝገብ የጀመረችው በትናንትናው እለት ነው
የፕሬዝደንት ኢብራሂም ሪይሲን ሞት ተከትሎ የቀድሞው የኢራን አፈጉባዔ ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር ተመዝግበዋል
የፕሬዝደንት ኢብራሂም ሪይሲን ሞት ተከትሎ የቀድሞው የኢራን አፈጉባዔ ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር ተመዝግበዋል።
አሊ ላርጃኒ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን የኢራኑን ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲን ለመተካት በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር በትናንትናው እለት ከተመዘገቡት ውስጥ ይገኙበታል።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ አማካሪ እና አጋር የሆኑት ላሪጃኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጠንካራ መከላከያ ከመገንባት ጎን ለጎን የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ላይ ያተኩራሉ።
ላርጃኒ እጩዎችን በሚመለምለው የሀይማኖታዊ ዘብ ምክርቤት በፈረንጆቹ 2021 በተካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ ተደርገው ነበር። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ላርጃኒ በድጋሚ ለመወዳደር የወሰኑት ወግ አጥባቂ በሆነው ምክርቤት ከውድድር ውጭ እንደማይደረጉ ማረጋገጫ በማግኘታቸው ነው። ምክርቤቱ አቋሙን የቀየረበት ምክንያት ግልጽ አልተደረገም።
ኢራን በፈረንጆቹ ሰኔ 28 እንዲካሄድ ቀን በተቆረጠለት ምርጫ የሚሳተፉ እጩዎችን መመዝገብ የጀመረችው በትናንትናው እለት ነው።
የኢራን ቁጥር አንድ ወሳኝ ሰው የሆኑትን አያቶላህ አሊ ካሚኒን ይተካሉ ተብለው የነበሩት ራይሲ ድንገኛ ሞት፣ የሀገሪቱን ሁለተኛ መሪ ለመተካት በወግ አጥባቂዎች መካከል ውድድር እንዲፈጠር አድርጓል።
ምዝገባው ካለቀ ከአምስት ቀናት በኋላ ምክር ቤቱ ለውድድር የሚቀርቡትን እጩዎች ይለያል። ለዘብተኛ የሆኑ ፖለቲከኞች ምክር ቤቱ ለወግ አጥባቂዎች ያዳላል የሚል ክስ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ።
ውስብስብ በሆነው በኢራን አስተዳደር ውስጥ ካሚኒ በኑክሌር፣ በውጭ እና በመሳሰሉት ወሳኝ ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን አላቸው። ነገርገን የሚመረጠው ፕሬዝደንት እየተባባሰ የመጣውን የኢኮኖሚ ችግር በመፍታት ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።
የቀድሞ የኑክሌር ተደራዳሪ እና ከሁለት አስርት አመት በፊት የካሚኒን ቢሮ ለአራት አመታት ሲመሩ የነበሩት ሰኢድ ጃሊሊ ሌላኛው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ተመዝጋቢዎች ውስጥ ናቸው።
ጃሊሊ በፈረንጆቹ 2013 በተካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተሳትፈው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከአራት አመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ደግሞ ራይሲን ለመደገፍ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል። የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ አባል የሆኑት ፓርቪዝ ፋታህ እና ጊዜያዊ ፕሬዝደንቱ ሞሀመድ ሞክበርም በምርጫው ለመሳተፍ ተመዝግበዋል።