ኢራን ለሚደርስባት ትንኮሳ ጠንካራ ምላሽ ትሰጣለች- ፕሬዝደንት ራይሲ
ራይሲ የኢራን ጦር የቀጠናውን ሰላም ከማስጠበቅ ውጭ ለማንም ስጋት ሆኖ እንደማያውቅ እና እንደማይሆን ተናግረዋል
የኢራኑ ፕሬዝደንት ራይሲ ኢራን ጦርነት እንደማትጀምር እና ትንኮሳ የሚደረግባት ከሆነ ግን ጠንካራ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ ኢራን ጦርነት እንደማትጀምር እና ትንኮሳ የሚደረግባት ከሆነ ግን ጠንካራ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህን ያሉት አሜሪካ በኢራቅ እና በሶሪያ ያሉ የኢራን ኢላማዎችን እንደምትመታ ከገለጸች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በጆርዳን ውስጥ በሶሪያ እና በኢራቅ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ታወር 22 በተባለው ኬላ ላይ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች በኢራን በሚደገፈው ካታይብ ሄዝቦላ መገደላቸውን ተከትሎ አሜሪካ ምን አይነት አጸፋዊ እርምጃ ትወስዳለች የሚለው ባለፈው ሳምንት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሮይተርስ እንደዘገበው አሜሪካ በኢራቅ እና በሶሪያ ያሉ የኢራን ይዞታዎችን እና ኃይሎችን ለመምታት የሚያስችላትን እቅድ አጽድቃለች።
ፕሬዝደንት ራይሲ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልእክት "ምንም አይነት ጦርነት አንጀምርም፣ ሊተነኩስን የሚፈልጉ ግን ጠንካራ ምላሽ ይጠብቃቸዋል" ብለዋል።
ራይሲ የኢራን ጦር የቀጠናውን ሰላም ከማስጠበቅ ውጭ ለማንም ስጋት ሆኖ እንደማያውቅ እና እንደማይሆን ተናግረዋል።
አሜሪካ ሶስት ወታደሮቿን የገደለው ድሮን የኢራን ድሮን ነው የሚል ክስ አቅርባለች።
የኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ከፍተኛ ኦፊሰሮችን ከኢራቅ እየወጡ መሆኑን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
አሜሪካ የመካከለኛውን ምስራቅ ሁኔታ ለመከታተል በሶሪያ እና በኢራቅ 3400 ወታደሮች አስፍራለች።