የዓለም ጤና ድርጅት 85 ሜትሪክ ቶን ህይወት አድን ድጋፎችን ለኢትዮጵያ ማድረጉን ገለፀ
የድርጅቱ ድጋፍ 150 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን መርዳት ያስችላል ተብሏል
ደርጅቱ ድጋፉን የሰጠው ዱባይ ካለው መጋዝኑ በአውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ በማጓጓዝ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት 85 ሜትሪክ ቶን ህይወት አድን ድጋፎችን ለኢትዮጵያ ማድረጉን ገለጸ።
ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ ድጋፍ ያደረገው በዱባይ ከሚገኘው መጋዝኑ ውስጥ ሲሆን በአውሮፕላን በማጓጓዝ ወደ ኢትዮጵያ ማድረሱን ገልጿል።
ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ ድርጅቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ለመርዳት የያዘው አቅድ አንዱ አካል መሆኑን በድረገጹ የወጣ መረጃ ያስረዳል።
ለኢትዮጵያ በድርጅቱ በኩል የተሰጠው ድጋፍ የህክምና ቁሳቁስ እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው ተብሏል።
ይህ የጤና ድጋፍ በተባበሩት ዓረብ ኢምሬት አውሮፕላን በተደረገ የአውሮፕላን ድጋፍ ወደ አዲስ አበባ መግባቱን ዘገባው አክሏል።
በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊ ዶክተር ቦሬማ ሳምቦ ድጋፉን አስመልክተው አንደተናገሩት በኢትዮጵያ በተፈጥሮ አደጋዎች፤በግጭቶች፤ በወረርሽኞች እና መሰል ምክንያቶች የጤና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ምከንያት አሁን ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሀላፊው በቀጣይ ከሌሎች የሰብዓዊ እና ጤና ተቋማት ጋር በመሆን ከ2 ነጠብ 5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።