እስራኤል በጋዛ የጤና ተቋማት ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጠየቁ
ዳይሬክተሩ እስራኤል ከአለም አቀፋዊ ህግ በተጻረር መልኩ ሆስፒታሎችን የጦርነት ሜዳ አድርጋለች ሲሉ ወቅሰዋል
ከሰሞኑ እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 260 ሰዎችን አስራለች
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ጤና ተቋማት ላይ ከምታደርገው ተደጋጋሚ ጥቃት እንድትቆጠብ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አሳሰቡ፡፡
ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ባለፉት ጥቂት ቀናት እስራኤል ሆስፒታሎችን ጨምሮ በተለያዩ ጤና ተቋማት ላይ ከምትፈጽመው ጥቃት በዘዘለ ተደጋጋሚ ድንገተኛ አሰሳዎችን በማድረግ የጤና ስርአቱን እያወከች ነው ብለዋል፡፡
በይፋዊ ኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “በጋዛ ያሉ ሆስፒታሎች የጦር ሜዳ ሆነዋል፤ የጤና ስርዓቱም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል” ነው ያሉት፡፡
በሆስፒታሎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር ቴዎድሮስ በጋዛ ውስጥ የሰብአዊ ድርጅቶች በቂ የጤና እርዳዎችን ለማድረግ እንዲችሉ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
እሁድ እለት በአል ዋፋ ሆስፒታል የተፈጸመው እና የ7 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ጥቃት የሀማስ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን እስራኤል ገልጻለች፡፡
የእስራኤል ወታደሮች አርብ ዕለት ከካማል አድዋን ሆስፒታል በደርዘን የሚቆጠሩ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ240 በላይ ፍልስጤማውያንን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንና ከነዚህም መካከል የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ሁሳም አቡ ሳፊያ እንደሚገኙበት የአካባቢው የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ሆስፒታሉ ለሃማስ ወታደራዊ ዘመቻ እንደ ማዘዣ ማዕከል እያገለገለ መሆኑን እና በቁጥጥር ስር የዋሉትም ታጣቂዎች ናቸው ብሏል።
የሀስፒታሉን ዳይሬክተር አቡ ሳፊያ በሃማስ ተላላኪነት እንደተጠረጠሩ ያስታወቀው ጦሩ ለጥያቄ መወሰዳቸውን ገልጿል።
የሀማስ ታጣቂዎች በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎችን እንደመከለያነት እየተጠቀማቸው ነው ሲል የእስራኤል ጦር በተደጋጋሚ ይከሳል፤ ሀማስ በበኩሉ ይህ ውንጀላ ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው ሲል ያስተባብላል፡፡
ባለፈው ሳምንት በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ አየር ማረፊያ ላይ እስራኤል ከፈጸመችው ጥቃት ለጥቂት ያመለጡት የአለም ጤና ድርጅት ሀላፊ አቡ ሳፊያ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ሆስፒታሎች ከሁሉም ተዋጊዎች ኢላማ ነጻ እንዲሆኑ የአለም አቀፍ ህግ እንደሚያስገድድ አስታውሰው “በጋዛ የሚገኝው የጤና ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አስከፊ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን” አመላክተዋል፡፡
የጥቅምት ሰባቱን የሀማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባወጀችው ጦርነት እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ንጹሀን ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ108 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት አስተናግደዋል፡፡