እስራኤል በሰንአ ኤርፖርት ድብደባ ስትፈጽም ዶክተር ቴድሮስ በስፍራው እንደነበሩ ገለጹ
በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ በተቃጣው ጥቃት በጥቂቱ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉና ከ30 በላይ መቁሰላቸው ተገልጿል
ኢራን፥ እስራኤል በየመን የፈጸመችው ድብደባ "የአለም ሰላምና ደህንነትን በግልጽ የጣሰ ነው" ብላለች
እስራኤል በየመን ሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ትናንት ጥቃት ስትፈጽም የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኤርፖርቱ ውስጥ እንደነበሩ ገለጹ።
ከሌሎች የመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞች ጋር አውሮፕላን ውስጥ ለመግባት ሲጠባበቁ ጥቃቱ መፈጸሙንም ነው ያነሱት።
ሃውቲዎች የሚያስተዳድሩት ሳባ የዜና ወኪል በሰንአ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሶስት ሰዎች መገደላቸውንና 30 መቁሰላቸውን ዘግቧል።
እስራኤል በምዕራባዊ ሆዴይዳህ በፈጸመችው ድብደባም ሶስት ሰዎች ተገድለው 10 የሚጠጉ ደግሞ ቆሰለዋልም ነው ያለው ዘገባው።
ዶክተር ቴድሮስ በኤክስ ገጻቸው ወደ የመን ያመሩት "የታሰሩ የተመድ ሰራተኞችን ለማስለቀቅ ድርድር ለማድረግና የሀገሪቱን የጤና ስርአት ለመመልከት" መሆኑን ገልጸው ጥቃቱ ከእርሳቸው በሜትሮች ርቀት ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የእስራኤልና የመን ፍጥጫ እያየለ መምጣት በቀጠናው ተጨማሪ ውጥረት እንደሚፈጥር በመጥቀስ "እጅግ አሳሳቢ ነው" ብለዋል።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል በየመን የፈጸመችው ድብደባ "አለማቀፍ ሰላምና ደህንነትን በግልጽ የጣሰ ነው" ነው በሚል ተቃውሞዋን ገልጻለች።
የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ የሃውቲ ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል ባላቸውና በደህንነት መረጃ በተለዩ ወታደራዊ ኢላማዎች የተሳካ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
ጦሩ በሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ "ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች" ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ቢጠቅስም ሲቪል መንገደኞች ከጥቃቱ ለማምለጥ ሲሯሯጡ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጥቃቱ በኋላ "የኢራን ክፉ አላማ አስፈጻሚዎች ላይ የጀመርነው ጥቃት ገና ጅምር ላይ ነው፥፡ እስከፍጻሜው እንገፋበታለን" ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የመከላከያ ሚኒስትራቸው እስራኤል ካትዝም የሃውቲ መሪዎች የሃማስና ሄዝቦላህ መሪዎች እጣ እንደሚገጥማቸው "ሁሉም ከእስራኤል ረጅም እጅ አያመልጡም" በማለት ዝተዋል።
ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለመግለጽ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችና ድሮኖችን የሚተኩሰው ሃውቲ በበኩሉ የትናንቱን ጥቃት "አረመኔያዊ" ሲል የገለጸው ሲሆን፥ በሃይል ጣቢያዎች እና ወደቦች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት አጻፋውን እንደሚመልስ ገልጿል።