መንግስት ስለጀመረው የጸረ ሙስና ዘመቻ የህግ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
ሙስና ብሄራዊ የደህንነት ስጋት ሆኗል ያለው መንግስት ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ከጀመረ ሰነባብቷል
በጸረ ሙስና ዘመቻው አካሄድ እና ሊተኮርባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል
ሙስና በረቀቀ መንገድ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አንዳንድ ጊዜም በሕጋዊነት ሽፋን ይፈጸማል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድም ሙስና ከኢትዮጵያ የጸጥታ ሥጋቶች እኩል እንቅፋት መሆኑን በህዳር ወር 2015 መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ጠ/ሚ ዐቢይ “ሙስና ከኢትዮጵያ የጸጥታ ሥጋቶች እኩል እንቅፋት ሆኗል” አሉ
የደህንነት ስጋት ነው የተባለውን ሙስና ለመዋጋትም ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስር ከጀመረ ሰነባብቷል።
ብሄራዊ ኮሚቴው በተለያየ ጊዜም በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ህብረተሰቡ ለኮሚቴው ጥቆማ እንዲሰጥም አድራሻዎች ይፋ ሆነዋል።
ጠበቃ እና የህግ አማካሪው ዶክተር መሳይ ሀጎስ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናሩት ሙሰኞችን አደብ ያስይዛሉ የተባሉት የፍትህ ተቋማት ጭምር የችግሩ አካል መሆናቸው መንግስት ኮሚቴ እንዲያቋቁም ማስገደዱን ይገልጻል፡፡
ህግን ማስከበር የመንግስት የእለት ተዕለት ስራ መሆን ሲገባው በዘመቻ መልክ በረቀቀ መንገድ የሚካሄዱ የሙስና ተግባራትን ለመግታት ማሰብ ግን ስህተት ነው ብለው ያምናሉ።
ሌላኛው ጠበቃና የህግ መምህሩ አቶ ቸርነት ሆርዶፋ ግን የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥረው ሀገርን የሚዘርፉ አካላት እጃቸው ረጅም መሆኑንና የዘረጉትን የጥቅም ትስስር መዘንጋት ተገቢ አይደለም ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
መንግስት የሙስናን የሀገር ደህንነት አደጋ ጠቅሶ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ትኩረት እንደሰጠው እንጂ ሙስናን አቅልሎ ማየቱን አያሳይም ባይ ናቸው።
መንግስት በከፍተና ባለስልጣናት ላይ እርምጃ አይወስድም የሚል ትችት ይነሳበታል፡፡
ኢትዮጵያ በጠራራ ጸሃይ መርከብና አውሮፕላን የሚጠፋባት፤ ህዝብ በስኳር እጦት እየተሰቃየ ጥቂቶች ቢሊየን ዶላሮችን ወደ ውጭ የሚያሸሹባት ሀገር መሆኗን የሚያነሱት ዶክተር መሳይ በዚህ ውስጥም በመንግስት መዋቅር የተሰገሰጉ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች እጃቸው ረጅምበኮሚቴ መፍታት እንደማይቻል ያነሳሉ።
ጠበቃና የህግ መምህሩ አቶ ቸርነትም በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ ባለስልጣናት እና ባለሃብቶችን በቁጥጥር ስር ማዋል ሀገር በሚመራው መንግስት ላይ የሚያመጣውን አደጋ ያብራራሉ።
“በሙስና ውቅያኖስ ውስጥ የተዘፈቁትና በተደራጀና በረቀቀ መንገድ የህዝብና የሀገር ሃብትን የሚመዘብሩትን አካላት መያዝ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ረገድ የሚያመጣውን አደጋ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። መንግስት ሙስና ብሄራዊ የድህንነት ስጋቴ ሆኗል ማለቱም ለዚሁ ነው ይላሉ።
“እነዚህን አካላት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠንካራ ስልጣንና ህዝባዊ ቅቡልነት ያስፈልጋቸዋል፤ ህዝባዊ ድጋፍ ከሌለም ትልልቆቹን ሙሰኞች መያዙ ብቻ ዘመቻውን ከግብ አያደርሰውም” የሚል ሃሳባቸውም ያክላሉ።
በግብታዊነት ሚኒስትሮችንም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ማዋል መንግስትን እስከመገልበጥ የደረሰ አደጋም ሊያስከትል ስለሚችል በጥናት ላይ ተመስርቶ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ነው ያብራሩት።
ዶክተር መሳይ ግን ስልጣን ላይ የሚቀመጡት አካላት የፓርቲ ታማኝነታቸው እስከተረጋገጠ ድረስ ጠያቂ እንደሌላቸው ያለፉት ሁለት ወራት የጸረ ሙስና ዘመቻ አሳይቶናል ባይ ናቸው።
መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበርና የህዝብን ሃብት የማፍራት መብት የእለት ተዕለት ስራው ካላደረገውና የሚያመጣውን አደጋ በመፍራት ትልልቆቹን በዝምታ ካለፋቸው የከፋ ቀውስ እንደሚከተልም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ከከፍተኛ የፌደራል አመራሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ፥ የሙሰናን አደጋ በስፋት ቢጠቅሱም ለመታወቂያ እና ለመንጃ ፍቃድ የሚጠየቁ መጠነኛ ወይም ፒቲ ኮራፕሽን እንጂ በብልጽግና መሩ መንግስት መዋቅራዊ መልክ የያዘ አለመሆኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ሙስና ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ አመራሩ ድረስ በተደራጀ መልኩ ተንሰራፍቶ ህዝቡን ማማራሩን ቀጥሏል ይላሉ የህግ ባለሙያዎቹ።
እጃቸው ረጃጅም የሆኑ የመንግስት ሹማምንት የግለሰቦችን መሬት እየነጠቁ ከመቸብቸብ ፍትህን እስከመሸጥ መድረሳቸው የአደባባይ ሚስጢር መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ጠንካራ ተቋም ወይስ ኮሚቴ?
ኢትዮጵያ “ሙስናን አናንቆጳጵሰው ፤ ሌብነት እንበለው፤ የተቀናጀ ዘመቻም እናድርግ” የማለቷን ያህል ጠንካራና ከስራ አስፈጻሚው የተላቀቀ ገለልተኛ ተቋም አልገነባችም የሚሉት ዶክተር መሳይ ሃገሪቱን ወደኋላ እየጎተተ ያለውን ስር የሰደደ ሙስና በዘመቻ ስራ ወይም በኮሚቴ መፍታት እንደማይቻል ያነሳሉ።
“ህግን ያስከብራሉ የተባሉ ተቋማት እጃቸው የመተሳሰሩና አንዳንዴም የጥቅም ተጋሪ መሆናቸው” ችግሩን እንዳሰፋውም ነው የሚያብራሩት።
የጸረ ሙስና አዋጁን ማስፈጸም ቢቻል፣ በፍትህ ሚኒስቴር ስር ያለው የሙስና ወንጀልን የሚከታተል ዳይሬክቶሬትም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ስራቸውን በአግባቡ ቢከውኑ ኮሚቴ ማዋቀር ባላስፈለገ ሲሉም ይገልጻሉ።
የህግ መምህሩ እና ጠበቃው አቶ ቸርነት ሆርዶፋ ግን መንግስት የጀመረውን የጸረ ሙስና ዘመቻ ለማጣጣል የሚሞክሩት ራሳቸው ሙሰኞቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያነሳሉ።
የመንግስትን ቅቡልነትና ህዝባዊ ድጋፍ በማሳጣት ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚሞክሩ አካላትን ፕሮፖጋንዳ ቸል በማለት በጥናት ላይ የተመሰረት እርምጃን መውሰድ እንደሚጋባም ያሰምሩበታል።
“በሩስያ ቭላድሚር ፑቲን፤ በቻይና ደግሞ ሺ ጂንፒንግ የተሳካ የጸረ ሙስና ዘመቻ ያደረጉት የማይንገዳገድ ጠንካራ ስልጣን ይዘውና ህዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው ነው” የሚሉት አቶ ቸርነት በየዘርፉ ጥልቅ ጥናቶችን በማድረግ የጸረ ሙስናውን ዘመቻ በጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የህግ ባለሙያዎች ህግ ያስከብራሉ የተባሉት ተቋማት ላይ የሚታየው ችግር ስር ሳይሰድ በቁጥጥር ስር ካልዋለ ሀገሪቱን ወደለየለት ስርአት አልበኝነት ሊያመራት እንደሚችል አሳስበዋል።
መንግስት የሚሾማቸው አመራሮችም ለህዝብና ለሀገራቸው ታማኝ የሆኑና በስራቸው አንቱታን ያተረፉ ከመሆቸው ይልቅ ለፓርቲ ያላቸው ታማኝነት ብቻ እየታየ ስርቆታቸው የሚሸፍንላቸው ከሆነ ተያይዞ መጥፋት መሆኑን ማስታውስም ተገቢ ነው ብለዋል።
አል አይን አማርኛ የጸረ ሙስና ዘመቻውን ከሚመራው ኮሚቴም ሆነ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ተጨማሪ ማብራሪያን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።