የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በተከሰሰቡበት የሙስና ወንጀል ምስክር መስማት ተጀመረ
ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጉቦ በመቀበል፣ በማጭበርበርና እምነት በማጉደል በሚል ነው የተከሰሱት
የ71 ዓመቱ ቤኒያሚን ኔታንያሁ የተከሰሱባቸውን ሙስና ወንጀሎች አልፈጸምኩም ሲሉ ተከራክረዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በተከሰሰቡበት ሙስና ወንጀል በዛሬው እለት ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተነገረ።
ቤኒያሚን ኔታንያሁ በተከሰሰቡበት ሙስና ወንጀል ላይም ምስክር የመስማት ሂደት የጀመረ ሲሆን፤ እስካሁን አንድ ምስክር መሰማቱንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የ71 ዓመቱ ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጉቦ በመቀበል፣ በማጭበርበር እና የተጣለባቸውን በማጉደል በሚባሉ ሶስት የተለያዩ ክሶች ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከተከሰሱባቸው ክሶች መካከልም፤ በምላሹ ውለታን ለመዋል ከአንድ የእስራኤል ባለሃብት በርካታ ሲጋራዎችን እና ሻምፓኝ መጠጦችን ተቀብለዋል እንዲሁም “የዲየት አህሮን” የተባለ ጋዜጣ ስለሳቸው በጎ ነገሮችን እንዲዘግብ እና በምላሹም ጋዜጣው ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ተደራድረዋል የሚሉ ይገኝበታል
ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ባሳለፍነው ወር በችሎት ፊት ቀርበው የተከሰሶባቸውን ጉዳዮች አልፈጸምኩም ሲሉ ተከራክረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የክስ ሂደት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዘው ተጥለው በነበሩ ክልከላዎች እና ባለፈው ወር በሀገሪቱ ከተካሄደው ምርጫ ጋር ተያይዞ ሲራዘም መቆየቱ ይታወሳል።
እስራኤል በ2 ዓመት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ ምርጫ ያደረገች ሲሆን፤ እስካን መንግስት ለመመስረት የሚስችል ድምጽ ያገኘ ፓርቲ የለም።
ይህንን ተከትሎም የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሬቨን ሪቭሊን አዲስ ጥምር መመስረት እድል ያላቸውን ፓርቲዎች ለማጨት በዛሬው እለት ከሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግስት እንዲመሰርቱ እድል ከተሰጣቸው ስልጣናቸውን ተጠቅመው ራሳቸውን ነጻ ሊያወጡ ይችላሉ ሲሉ ልሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።