የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ
የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ስራ በመግባት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ
በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ250 በላይ ጥቆማዎች ቀርበው እያጣራ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋ
የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ስራ በመግባት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ።
የሀገር ደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ለመከላከል ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መቋቋሙ ይታወሳል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነህ እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ የኮሚቴውን ስራዎች ክንውን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኮሚቴው የተቋቋመው የሁሉም ተቋማት መረጃ ወደ አንድ ቋት መጥቶ እንዲሰራበት በማስፈለጉ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሶስት ንዑስ ኮሚቴ ተቋቋሞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው፤ የመረጃ መቀበል ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም በየተቋማቱ ጥናቶች ማሰባሰብ እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል።
ዶክተር ጌዴዎን በበኩላቸው፤ የመሬት አስተዳደር፣ የፀጥታና ፍትህ፣ ጉምሩክ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልፀው፣ በተለይ የመሬት አስተዳደር እና በፍትህና ፀጥታ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
በልማት ተነሺ ስም በሀሰተኛ ሰነድ መሬት የሰጡ ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ 175 ሺህ ካሬ መሬትና ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የመዘበሩ፣ የኮንዶሚኒየም ቤት የመዘበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ገልፀዋል።
በፍትህና ፀጥታ ዘርፍ ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ከግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘብ የተቀበሉ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም እንዲሁ።
በዚህም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ የተለያዩ የፍትህና ፀጥታ የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የክስ ምስረታ ሂደት ላይም መሆኑን ገልፀዋል።
በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ250 በላይ ጥቆማዎች በተለያዩ መንገዶች ቀርበው ማጣራት እየተከናወነባቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በክልሎችም ከትንሽ እስከ ከፍተኛ የተደራጀ ሌብነት ተሳታፊዎች ተጠያቂነት የማስፈኑ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።