የዓለም ንግድ ድርጅትን እንዲመሩ የተመረጡት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ማን ናቸው?
የቀድሞዋ የናይጄሪያ የፋይናንስ ሚኒስትር ከመጪው መጋቢት 1 (እ.አ.አ) ጀምሮ ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት ይመራሉ ተብሏል
ናይጄሪያዊቷ ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዊዓላ (ዶ/ር) የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመርጠዋል
ናይጄሪያዊቷ ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዊዓላ (ዶ/ር) የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመረጡ፡፡
ኢዊዓላ ዓለም አቀፉን ተቋም እንዲመሩ የተመረጡት ድርጅቱ ዛሬ ባካሄደው ልዩ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ነው፡፡
የቀድሞዋ የናይጄሪያ የፋይናንስ ሚኒስትር ከመጪው መጋቢት 1 (እ.አ.አ) ጀምሮ ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት ይመራሉ ተብሏል፡፡
ይህም ኢዊዓላ ተቋሙን ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያዋ ሴት እና የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ያደርጋቸዋል፡፡
ድርጅቱን ለመምራት የቻሉ 7ኛዋ ሰውም ናቸው ኢዊዓላ፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለደረሱ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት ከአባል ሃገራቱ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ተቀዳሚ የቤት ስራቸው እንደሚሆንም ሹመታቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ዓለምን ሊለውጥ የሚችል ዐቅም እንዳለው ሆኖም ሪፎርም ሊደረግ እና አሰራሮቹ ሊፈተሸ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ መሪ የሚመረጠው ከ160 በሚልቁት አባል ሃገራት ስምምነት ነው፡፡ የዋና ዳይሬክተርነቱን ቅድመ ግምት አግኝተው የነበሩት ኢዊዓላም የአባል ሃገራቱ ድጋፍ ነበራቸው፡፡
ሆኖም የአሜሪካ ድጋፍ አልነበራቸውም፡፡ ምንም እንኳን የአሜሪካ ዜግነት ቢኖራቸው የተሰናባቹን ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርን ድጋፍ አላገኙም ነበር፡፡
የትራምፕ አስተዳደር ከእሳቸው ይልቅ ደቡብ ኮሪያዊቷን ዮ ሚዩንግ ሂን ይደግፍ ነበር፡፡
በዚህም ድርጅቱ በራሳቸው ፈቃድ ከኃላፊነት የለቀቁትን ብራዚላዊውን ሮቤርቶ አዝቬዶን ሊተካ የሚችል ሰው በቶሎ ሳያገኝ እንዲቆይ ሆኗል፡፡ ካሳለፍነው ወርሃ ነሃሴ ጀምሮም ዋና ዳይሬክተር አልነበረውም፡፡
አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር ግን ከዮ ሚዩንግ ሂን ይልቅ ኢዊዓላን በመደገፉ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሊመረጡ ችለዋል፡፡
ለመሆኑ ዓለም አቀፉን ተቋም እንዲመሩ የተመረጡት ኢዊዓላ ማን ናቸው?
የ67 ዓመቷ ኢዊዓላ እ.አ.አ በ1954 ነው ያኔ ሃገራቸው ናይጄሪያ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ጊዜ የተወለዱት፡፡
የመጀመሪያና የሁተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሃገራቸው ከተማሩ በኋላም በ1973 ወደ አሜሪካ አቅንተው ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም በ1981 ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ በልማታዊ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡
ኢዊዓላ ለ25 ዓመታት ያህል የዓለም ባንክን በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በባንኩ የስልጣን እርከን ሁለተኛ ሰው እስከመሆን ደርሰውም ነበረ፡፡
የናይጄሪያ የፋይናንስ ሚኒስትር በመሆንም በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ሃገራቸውን አገልግለዋል፡፡
ይህ የሆነው በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና በጉድላክ ጆናታን የፕሬዝዳንትነት ዘመን ነው፡፡
ይህም በሁለት የተለያዩ ፕሬዝዳንቶች የስልጣን ዘመን ሃገራቸውን በፋይናንስ ሚኒስትርነት ያገለገሉ የመጀመሪያዋ ናይጄሪያዊ ያደርጋቸዋል፡፡