“ጃዋር ‘መንግስት ከዳኝ’ የሚል አቋም አለው”- መረራ ጉዲና (ፕ/ር)
“መንግስት ላቀረብናቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ባልሰጠበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባቱ ትርጉም የለውም” ሲሉም ነው አንጋፋው ፖለቲከኛ የሚናገሩት
የኦፌኮው ሊቀመንበር የኢሶዴፓን መድረክ ከተሰኘው ጥምረት መውጣት ከሚዲያዎች መስማታቸውንም ገልጸዋል
በመጪው ሃገራዊ ምርጫ ለመወዳደር ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ “አላግባብ ታስረውብኛል” የሚላቸው ከፍተኛ አመራሮቹ ጉዳይ እንደሆነ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስታወቀ፡፡
ኦፌኮ ከምርጫው በፊት ሊመለሱልኝ የሚገቡ አምስት መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉኝም ብሏል፡፡
መሰረታዊ ከተባሉት ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱ “አላግባብ የታሰሩ” የፓርቲው አመራሮች ጉዳይ እንደሆነ ከሰሞኑ ከአል አይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡
አመራሮቻችን የታሰሩበት ምክንያት “አላሳመነንም አያሳምነንምም” የሚሉት ሊቀመንበሩ “እንዴት እንደታሰሩ እኛም መንግስትም ጨዋታውን እናውቃለን” ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
አመራሮቹ “አላግባብ ነው የታሰርነው” የሚለውን ይህን አቋማቸውን ለማንጸባረቅ በርሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ አድማው መንግስት ላይ ጫና ለማድረግ ጭምር በማሰብ የሚደረግ ነውም ይባላል፡፡ ኦፌኮም ሁኔታውን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ይህ ቃለ መጠይቅ በተደረገበት ወቅትም ፓርቲው ስብሰባ ላይ ነበረ፡፡ ስብሰባው በዚሁ ጉዳይ ላይ ማተኮሩን የገለጹት ፕ/ር መረራም “እኔም የርሃብ አድማ ያደረጉ አመራሮቻችን እንዲበሉ ለመምከር ወደ ታሰሩበት ሄጄ ነበር” ብለዋል፤ ጉብኝታቸው ሳይሳካ መመለሳቸውን በመግለጽ፡፡
አሁንም “በተቻለ መጠን [እስረኞቹን] ለመምከር እንፈልጋለን” የሚሉት ሊቀመንበሩ “ሆኖም ሳያመሩ አልቀረም” ይላሉ፡፡ “በሃቅ አይደለም የታሰርነው” እንደሚሉም ነው የሚናገሩት፡፡
“ጃዋር ከውጭ እንዴት እንደመጣ ይታወቃል፡፡ ‘ለውጥ መጥቷል ብዬ ለውጡን ለማገዝ መጥቼ እንዴት እንደዚህ እደረጋለሁ መንግስት ከዳኝ’ የሚል አቋም አለው” በሚልም ያስቀምጣሉ፡፡
“እኛ ችግሮች ቢኖሩም እንዲበሉ እንፈልጋለን በዚህ መንገድ እንዲሞቱብን አንፈልግም ይሄንንም ለሁሉም አሳውቀናል” ይላሉም አንጋፋው ፖለቲከኛ፡፡
የሰኔ 22ቱን የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ካጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ ለእስር ከተዳረጉ ሰዎች መካከል የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እና ፓርቲውን በቅርቡ የተቀላቀሉት አቶ ጃዋር መሃመድ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አባላትና አመራሮችም ታስረውብኛል ይላል ኦፌኮ፡፡
ይህ “ጎድቶናል” የሚሉት ፕ/ር መረራ መንግስት ይህን ጨምሮ አሉን ለሚሏቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
መንግስት ያን ባላደረገበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባቱ ትርጉም የለውም ሲሉም ነው የሚናገሩት፡፡
ኦፌኮ በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበው በ2001 ዓ/ም “መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ/ መድረክ” የሚል ጥምረትን ከመሰረቱ 6 ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ም ጥምረቱን ከመሰረቱ ነባር ፓርቲዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ ሆኖም ከጥምረቱ መውጣቱን አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢሶዴፓ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ኦፌኮ “ከጥምረቱ ህገ ደንብ ውጭ” ያደርጋቸዋል ያሏቸውን እንቅስቃሴዎች ነው በምክንያትነት ያስቀመጡት፡፡
ፕ/ር መረራ ግን “ስለ ጉዳዩ አናውቅም” ብለዋል ኢሶዴፓ ጥምረቱን ለቆ ስለመውጣቱ ያሳወቃቸው ነገር እንደሌለ በመጠቆም፡፡
ከጥምረቱ ስለመውጣቱ ከሚዲያዎች መስማታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
‘ተባብረው ለመስራት ተስማሙ’ ሲባል ቆይቶ አሁን ደግሞ ‘ተለያዩ’ መባሉን ባለመፈለጋቸው ምክንያት ስለጉዳዩ በዝርዝር መናገር እንደማይፈልጉም ተናግረዋል የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ፡፡
ፕ/ር በየነ “ኦፌኮ በጣም አጨቃጫቂ፣ አከራካሪ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስጋት ውስጥ የሚከት ፕሮፖጋንዳ ውስጥና ህዝብን ማነሳሳት ውስጥ የሚገቡ ሰዎችን በአባልነት መቀበሉ” ለኢሶዴፓ ከጥምረቱ መውጣት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“እንደዚህ የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ”ሲሉ ለጉዳዩ ምላሽ የሚሰጡት ፕ/ር መረራ ግን “የዚህ ሃገር ፖለቲካ ትልቁ ችግር ‘ቡዳው’ ማን እንደሆነ በግልጽ አለመታወቁ ነው” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
ይህ “ተጣርቶ እስካልታወቀ ድረስ ማንም ማንንም ሊከስ አይችልም” የሚሉም ሲሆን በጽንፈኛ አቋማቸው የሚጠቀሱ የፓርቲው አባላትና አመራሮች በመንግስት ጥሪ በግልጽ ወደሃገር መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡
ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድም ጥሪ አቅርበዋል፡፡