“የፓርቲው ‘ማኒፌስቶ’ ከሕዝባችን ጋር የምንገባው ኮንትራት ሳይሆን ቃል ኪዳን ነው” የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ
ብልጽግናን ጨምሮ የ49 ፓርቲዎች ምልክት በቦርዱ ይፋ ቢሆንም በምርጫው መሳተፋቸውን እርግጠኛ ያልሆኑ ፓርቲዎች አሉ
ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶውንና የመወዳደሪያ ምልክቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል
የምርጫ 2013 የብልጽግና ፓርቲ ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት "ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳበ ይፋዊ የእውቅና መድረክ በሸራተን አዲስ ተካሂዷል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚደንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፓርቲውን ‘ማኒፌስቶ’ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ ሲያደርጉ “የፓርቲው ‘ማኒፌስቶ’ ከሕዝባችን ጋር የምንገባው ኮንትራት ሳይሆን ቃል ኪዳን ነው” ብለዋል።
ይህ ቃል ኪዳን እውን እንዲሆን “እያንዳንዱ የብልጽግና አባል በፍፁም ፈቃደኝነት ራሱን በመስጠት አገልጋይ መሆን” እንደሚጠበቅበትና ከሕዝቡም ድጋፍ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል።
“የፓርቲው ‘ማኒፌስቶ’ ድርሰት ሳይሆን ከአንድ ዓመት በላይ መረጃ በመሰብሰብና ከሕዝቡ ጋር በመወያየት የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት የተዘጋጀ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት።
ፓርቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ መምጣቱን ጠቅሰው ከብዙ መከራና ፈተና በተግባር እየተማረ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዝደንት አብራርተዋል።
“ብልፅግና መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ እንደሚቻል ያሳየ ስብስብ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህም የሕዳሴ ግድብን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ፣ የሸገር ፣ የእንጦጦ እንዲሁም የአንድነትና የመስቀል አደባባይን ጨምሮ ሌሎች በስኬት የተጠናቀቁ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በኢኮኖሚ፣ በእርሻ፣ በቱሪዝምና ሌሎች መስኮች የተከወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያሳዩ መምጣታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ስራዎችን ማስፋት ከተቻለ "ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ማማ ትወጣለች" ብለዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማድረስ የሚቻለው የተረኝነት አስተሳሰብን በማስወገድ በአንድ ልብ ተሳስሮ በጋራ መቆም ሲቻል ብቻ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ “ብልጽግና መሠረት የሚጥል” መሆኑንም ተናግረዋል።
ምርጫውን ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በማድረግ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አሸናፊ የሚሆኑበት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ኢዜአ እንደዘገበው ለምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ መጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 28 ይካሔዳል፡፡ በምርጫው ለመወዳደር ከተመዘገቡ ፓርቲዎች መካከል 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምልክት በምርጫ ቦርድ ይፋ ተደርጓል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በምርጫው ስለመሳተፋቸው እርግጠኞች አይደሉም፡፡ ከነዚህ መካከል ኦነግ እና ኦፌኮ ይጠቀሳሉ፡፡
የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀጄላ መርዳሳ ፣ በፓርቲው ክፍፍል ምክንያት ኦነግ ዝግጅት አለማድረጉን እና በምርጫው የመሳተፍ ዕድሉ 50 በመቶ መሆኑን ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
የኦፌኮ ፕሬዝደንት መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ደግሞ ፣ መንግስት በፓርቲያቸው የተጠየቁ ጥያቄዎችን ካልመለሰ በምርጫው ለመወዳደር እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች መካከል በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች እንዲፈቱ የቀረበው ይገኝበታል፡፡