በእስራኤል የሚፈለገው አዲሱ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነው?
የጥቅምት 7 ጥቃት ዋነኛ መሪ የሆነው ሲንዋር እስራኤል ልትገድላቸው ከምትፈልጋቸው ሰዎች መካከል ቁጥር አንዱ ሆኗል
የ61 ዓመቱ ሲንዋር በጋዛ ዋሻዎች የእስራኤል ጦርን የሚደረጉ ውጊያዎችን እየመራ ነው ተብሏል
በእስራኤል የሚፈለገው አዲሱ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነው?
ከ10 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ምድር ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
1 ሺህ 200 ሰዎች በሐማስ ጥቃት ተገድለውብኛል ያለችው እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የድርጅቱ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎችን ገድላለች።
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ያልተጠበቀ ጥቃት ከሀሳብ ማመንጨት ጀምሮ ጥቃቱን እንደመራ የሚታመነው ያህያ ሲንዋር አዲሱ የሐማስ መሪ ተደርጎ ተመርጧል።
ያህያ ሲንዋር በጋዛ እስላሚክ ዩንቨርስቲ እንደተማረ ሲገለጽ በእስራኤል እስር ቤቶች ለ23 ዓመታት መታሰሩ ተገልጿል።
ሲንዋርን ለእስር የዳረገው ሶስት የእስራኤል ወታደሮችን ገድሏል በሚል ሲሆን በፈረንጆቹ 2011 ላይ በተደረገ የእስረኛ ልውውጥ ሊፈታ ችላል።
ሒብሪው ቋንቋ አቀላጥፎ መናገሩ ስለ እስራኤል ባህል በሚገባ እንዲያውቅ ረድቶታል ተብሏል።
ዝምተኛ ነው የሚባለው ሲንዋር የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ እስራኤልን ለመመከት የዋሻ ውስጥ ውጊያዎችን እየመራ እንደሆነም ተገልጿል።
እስራኤል አሁን ላይ መግደል ከምትፈልጋቸው ሰዎች መካከል ቁጥር አንዱ ያህያ ሲንዋር እንደሆነም ተገልጿል።
በጋዛ ዋሻዎች ውስጥ በመሆን ከእስራኤል ጋር እየተደረገ ያለውን ውጊያ እየመራ እንደሆነ የሚገለጸው ያህያ ሲንዋር የእስራኤላዊያንን ስነ ልቦና እና ባህል በሚገባ የሚያውቅ ሰው ነው ተብሎለታል።
አሜሪክል በፈረንጆቹ 2015 ላይ ያህያ ሲንዋርን በዓለም አቀፍ ሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ በማካተት መያዝ ከምትፈልጋቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አካተዋለች።