የዴሞክራቷ እጩ ካማላ ሃሪስ አጣማሪ አድርገው የመረጧቸው ቲም ዋልዝ ማን ናቸው?
ሃሪስ እና ምክትላቸው ዋልዝ በትላንትናው እለት ለመጀመርያ ጊዜ በፊላዴልፊያ በጋራ የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምረዋል
ቲም ዋልዝ ለ24 አመታት በወታደርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል
የዴሞክራቷ እጩ ካማላ ሃሪስ በ2024 ምርጫ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚያጣምሯቸውን የሜኔሶታ አስተዳዳሪ ቲም ዋልዝን መርጠዋል፡፡
ሁለቱ ተወዳዳሪዎች የህዳሩን ምርጫ አሸናፊ ይወስናሉ ከሚባሉ የፍልሚያ ግዛቶች አንዱ በሆነው የፊላዴልፊያ ግዛት ለመጀመርያ ጊዜ በጋራ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡
በነብራስካ የተወለዱት የ60 አመቱ ቲም ዋልዝ ቀደም ሲል በመምህረነት እና በወታደርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
ወደ ፖለቲካው ከገቡ በኋላ ከ2007 እስከ 2019 በኮንግረሱ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ሰርተዋል። በ2019 እና በ2022 የሚኒሶታ አስተዳዳሪ ሆነው ለሁለት ጊዜ መመረጥ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የዴሞክራት አስተዳዳሪዎች ህብረት ሊቀመንበር ናቸው፡፡
በ17 አመታቸው በሀገሪቱ መከላከያ ናሽናል ጋርድ ውስጥ የተቀላቀሉት ቲም በጦሩ ውስጥ ለ24 አመታት አገልግለዋል። ከሚሊታሪ ህይወት እራሳቸውን ካገለሉ በኋላ በአሜሪካ ደቡብ ዳኮታ እና ሚኒሶታ እንዲሁም በቻይና በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስተመርዋል፡፡
ወደ ፖለቲካው አለም መሳብ የጀመሩት ማሳቹስቴት ግዛት ሴናተር ጆን ኬሪ በ2004 የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ከተቀላቀሉ በኋላ ነበር፡፡
በግዛት አስተዳዳሪነት ዘመናቸው የኮሌጅ የትምህርት ወጪን መሸፈን ለማይችሉ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም በሚኒሶታ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የቁርስ እና የምሳ ምገባ በነጻ እንዲጀመር ያስቻሉ ናቸው፡፡
በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቋማቸው የኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነት ላይ የፈንድ ድጋፍ እንዲደረግ በኮንግረሱ እና በሌሎች ማዕቀፎች ቅስቀሳ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
በተጨማሪም በአሁኑናዊው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ለዩክሬን ድጋፍ ማድረግ የሩሲያን ተጽእኖ ለመግታት ወሳኝ ነው ብለው የሚያምኑ ሰው ናቸው።
ሃሪስ በአጣማሪነት ሊመርጧቸው እንደሚችሉ ከተዘረዘሩ ከ7 በላይ እጩዎች ቲምን ለምን እንደመረጧቸው ተንታኞች ሲናገሩ፤ ሰውየው በመከላከያው እና በሲቭል አገልግሎት በነበራቸው አበርክቶ በዜጎች ዘንድ ተወዳጅ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ወግ አጥባቂ ከሚባሉ ፖለቲከኞች እና መራጮች ጋር ቲም ያላቸው ወዳጅነት ዴሞክራቶችን በምርጫው ሊያግዝ የሚችል ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም የዴሞክራት እና ሪፐብሊካኖች በእኩል ቁጥር በሚገኙባት ሜኔሶታ ያለቅሬታ ማስተዳደር መቻላቸው ጥሩ የፖለቲካ ልምድ እንዲያካብቱ እንዳገዘቸውም ይነገራል፡፡
በተጨማሪም ቲም ከሰዎች ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት እና በንግግር የማሳመን ተጽእኗቸው በምርጫው ወሳኝ እጩ መሆናቸውን የሚያረገግጥ ነው ተብሏል፡፡