ማይክ ፔንስ እና ተቀናቃኛቸው ካማላ ሀሪስ ኮሮና ላይ ያተኮረ ክርክር አደረጉ
ለምርጫው 26 ቀናት ሲቀሩ በቅድመ ምርጫ ውጤቶች ባይደን በጠባብ ልዩነት ይመራሉ
ሁለቱ ተቀናቃኞች በኮሮና ስጋት ሳቢያ በመስታወት ተከልለው ነው የተከራከሩት
ማይክ ፔንስ እና ተቀናቃኛቸው ካማላ ሀሪስ ኮሮና ላይ ያተኮረ ክርክር አደረጉ
ኋይት ሀውስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ሚሊዮኖችን ያጠቃውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚታገልበት ወቅት ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እና የዴሞክራቶች ተፎካካሪው ካማላ ሀሪስ ትናንት ረቡዕ ምሽት ባደረጉት የምክትል ፕሬዝዳንት ዕጩ ክርክር በትራምፕ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አያያዝ ላይ አትኩረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በትራምፕ እና በዴሞክራቶቹ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ተወዳዳሪ ጆ ባይደን መካከል ከተካሔደው ዘለፋ የበዛበት ክርክር አንጻር የምክትል እጩዎቻቸው የማታው ክርክር የተረጋጋ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የባይደን ክርክር በትራምፕ የማያቋርጥ ጣልቃ-ገብነት እና በሁለቱም ሰዎች ግላዊ ዘለፋዎች የተሞላ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ክርክሩ በሶልት ሌክ ሲቲ በሚገኘው የዩታ ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር “በሀገራችን የፕሬዚዳንታዊ አስተዳደር ታሪክ ትልቁን ውድቀት የአሜሪካ ህዝብ ተመልክቷል” በማለት ሀሪ የትራምፕን አስተዳደር በጅምላ በመተቸት ነው ክርክራቸውን የጀመሩት፡፡
ፔንስ በምላሹ ለቫይረሱ መስፋፋት ቻይናን ተጠያቂ በማድረግ የትራምፕ አስተዳደር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት በማወደስ ተከራክረዋል፡፡
“ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለአሜሪካ ጤና ቅድሚያ መስጠታቸውን የአሜሪካ ህዝብ እንዲያውቅ እፈልጋለሁ” ያሉት ፔንስ አክለውም “ለኮሮናቫይረስ ቻይና ተጠያቂ ናት” ብለዋል፡፡
በቫይረሱ ስጋት ሳቢያ ሁለቱ ተቀናቃኞች ክርክራቸውን ያደረጉት በ 12 ጫማ (3.6 ሜትር) ተራርቀው እና በመስታወት ተከልለው ነው፡፡
ለፕሬዚዳንታዊ ዕጩነት የራሷን ያልተሳካ ውድድር ያደረገችው ሀሪስ በሕይወቷ ትልቁን የፖለቲካ ደረጃ ላይ ስትደርስ ከፍተኛ ጫና አጋጥሟት ነበር፡፡ ረቡዕ ምሽት ከፔንስ ጋር በነበራቸው ክርክርም በአብዛኛው ተሳክቶላታል እንደ ሮይተርስ ዘገባ፡፡
በ90 ደቂቃው ክርክራቸው ኮሮና ቫይረስ ዋነኛ አጀንዳቸው ቢሆንም በሌሎች ነጥቦች ላይ ተከራክረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የዘረኝነት ጉዳይ ፣ የትራምፕ በአመት ውስጥ 750 ዶላር ብቻ የፌዴራል ገቢ ግብር መክፈል ጉዳይ ፣ የአሜሪካ እና የቻይና የንግድ ጦርነት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የ74 ዓነቱ ትራምፕም ይሁን የ77 ዓመቱ ጆ ባይደን ውድድሩን ካሸነፉ ሁለቱም በአሜሪካ የእስካሁን ታሪክ በእድሜ ትልቅ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ፡፡
የቅድመ ምርጫ ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ለምርጫው 26 ቀናት በሚቀሩበት በአሁኑ ወቅት ውጤቱን በሚወስኑ ግዛቶች በጠባብ ልዩነት ይመራሉ፡፡