ቤልጅየም እና ዩክሬን የተደለደሉበት ምድብ 5 ሁሉም ቡድኖች በእኩል 3 ነጥብ ብርቱ ፉክክር እያደረጉ ነው
በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ጥሎ ማለፉን ለመቀላለቀል የሚደረገው ብርቱ ፉክክር ቀጥሏል፡፡
እስካሁን 4 ቡድኖች 16ቱን መቀላቀላቸውን ሲያረጋግጡ ቀሪውን ስፍራ ለመያዝ ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ቀናት የሚደረጉ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው፡፡
በስድስቱ ምድብ ውስጥ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች በቀጥታ ጥሎ ማለፉን ሲቀላቀሉ ቀሪ 4 ቡድኖች ደግሞ ምርጥ ሶስተኛ በመሆን ወደ 16ቱ ውስጥ ለመቀላቀል ይፎካከራሉ፡፡
በምድብ አንድ የሚገኙት ጀርመን እና ሲውዘርላንድ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ምሽት ላይ ሲውዘርላን እና ጀርመንን ያገናቸው የመጨረሻው የምድብ ጨዋታ በሲውዘርላንድ መሪነት እስከ ጭማሪ ደቂቃ አምርቶ፤ ፉልክሩጉ ባለቀ ሰአት ያስቆጠራት ግብ ጀርመን በ7 ነጥብ መሪነቷን አስቀጥላ ወደ ጥሎ ማለፉ እንድትቀላቀል አግዟል፡፡
በመክፈቻው ጨዋታ በጀርመን 5ለ1 ተሸንፋ አጀማመሯ ያላማረው ስኮትላንድ በሀንጋሪ በደረሰባት ሽንፈት ከውድድሩ ቀዳሚዋ ተሰናባች ሀገር ሆናለች፡፡ ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ የማለፍ እድል ያላት ሀንጋሪ እጣፈንታዋን ለማወቅ ቀሪ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎችን ውጤት ትጠብቃለች፡፡
የሞት ምድብ በተባለው ምድብ ሁለት መሪነቷን በ6 ነጥብ ያስቀጠለችው ስፔን ዛሬ ምሽት ቀሪ የምድብ ጨዋታዋን ከአልባኒያ ጋር ታደርጋለች። ምሽት 4 ሰአት ላይ ክሮሽያን የምትገጥመው ጣሊያን በምድቡ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የጨዋታው አሸናፊ 16ቱን መቀላቀሉን የሚያረጋግጥ ሲሆን ጣሊያንን አቻ ብትወጣም ቀደም ብላ የሰበሰበችው ውጤት ጥሎ ማለፉን እንድትቀላቀል ያስችላታል፡፡
በአንጸሩ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በአንድ ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ ላይ የሚገኙት ክሮሽያ እና አልቢኒያ የምሽቱ ጨዋታ የአውሮፓ ዋንጫ ቆይታቸውን የሚወስን ነው፡፡
በምድብ ሶስት የሚገኙት እንግሊዞች 16ቱን ለመቀላቀል ነገ ስሎቫኒያን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ከሰርቢያ ጋር የምትጫወተው ዴንማርክ ማሸነፍ ከቻለች የምድቡን መሪነት ከእንግሊዝ ተረክባ ጥሎ ማለፉን የምትቀላቀል ይሆናል፡፡
ዴንማር የምትሸነፍ ከሆነ እንግሊዞች ከስሎቫኒያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ቢሸነፉም ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ በእኩል ነጥብ በሚገኙበት ምድብ 4 ጥሎ ማለፉን የሚቀላቀሉ ቡድኖችን የሚለዩት ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ፡፡
በዚህ ምድብ ከአንድ እስከ ሶስት በደረጃ የሚገኙት ቡድኖች የሚለያዩት በአንድ ነጥብ መሆኑን ተከጥሎ የነገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድ የምድቡን የበላይነት ይዞ ለማጠናቀቅ ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል፡፡
በምድቡ 3 ነጥቦችን በመያዝ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝው ኦስትሪያ ኔዘርላንድን ማሸነፍ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ያደርጋታል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አራቱም ቡድኖች በእኩል 3 ነጥብ ላይ የሚገኙበት ምድብ 5 ቡድኖች እሮብ በሚያደርጉት ጨዋታ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ግዴታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምድቡን አላፊ እና ደረጃ ለመለየት ምድብተኞቹ ነገ የሚያደርጉት ሁሉም ጨዋታ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡
በመጨረሻው ምድብ የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሀገር ፖርቹጋል 16ቱ ውስጥ መግባቷን ያረጋገጠች ሌላኛዋ ሀገር ነች። በነገው እለት በምድቡ መጨረሻ ደረጃ ላይ ከምትገኝው ጆርጂያ ጋር የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዋን ታደርጋለች፡፡
ቱርክ ሁለተኛ ደረጃዋን አስጠብቃ ወደ ቀጣዩ ዙር ለመቀላቀል ስትጫወት ቼክሪፐብሊክ ቱርክን አሸነፋ ደረጃዋን ለመንጠቅ ካልሆነም በአቻ ውጤት ለምርጥ ሶስተኛነት ቦታ ትፋለማለች፡፡
ኦስትሪያ ፣ ስሎቫኪያ ፣ ሀንጋሪ ፣ ስሎቫኒያ ፣ አልባኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በምርጥ ሶስተኛነት ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል እድል ያላቸው ሀገራት ናቸው።