ትራምፕ የዩክሬንን ወታደራዊ እርዳታ ማቆማቸውን ተከትሎ ማን ምን አለ?
ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረገውን ሁሉንም ወታደራዊ እርዳታ ያቋረጡት ከፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ነው

ይህ የትራምፕ እርምጃ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ያሰፋዋል ተብሏል
ትራምፕ የዩክሬንን ወታደራዊ እርዳታ ማቆማቸውን ተከትሎ ማን ምን አለ?
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በኃይትሀውስ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ እርዳታ ማቋረጣቸውን የኃይትሀውስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ይህ የትራምፕ እርምጃ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ያሰፋዋል ተብሏል።
በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ከፍተኛ የዲሞክራት ባለስልጣናት የሆኑት የአሜሪካ ሴናተር ጄይኒ ሻሂን፦
"ፕሬዝደንት ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ በማቆም ፑቲን በንጹሃን ዩክሬናውያን ላይ የሚያደርገውን ጥቃት እንዲያጠናክር በሩን በሰፊው ከፍተውለታል። ውጤቱ ያለጥርጥር የከፋ ይሆናል።"
የእንግሊዝ መንግስት ቃል አቀባይ፦
"በዩክሬን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ቁርጠኞች ነን፤ ይህን ጥረት ለማጠናከር ከአጋሮቻችን ጋር እየተነጋገርን ነው። ይህ ትክክለኛ ነገረ ነው፤ ይህን ማድረግ የእኛ ፍላጎት ነው።"
የፈረንሳይ የአውሮፓ ጉዳይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ሀዳድ፦
"በመሰረቱ ሰላም ከፈለክ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እርዳታ ማቋረጥ ሰላም እንዲመጣ ያደርጋል ወይስ ያርቃል? ወራሪዋን ሩሲያን ስለሚያጠናክር የበለጠ እንዲርቅ ያደርገዋል" ሲሉ ፈረንሳይ ቱ ለተባለው ጣቢያ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዩክሬን ፓርላማንት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ ኦሌክሳንደር መሬዝኮ፦
"ከላይ ሲታይ መጥፎ ይመስላል። የሩሲያን ፍላጎትን እንድንቀበል እየገፋን ይመስላል። አሁን እርዳታ ማቋረጥ ፑቲንን መርዳት ማለት ነው።"
የፖላንድ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር፦
ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እርዳታ ማቋረጥ "መጥሮ ዜና ነው"ሲሉ ተናግረዋል።
የሀንጋሪ መንግስት ቃል አቀባይ፦
"የአሜሪካ ፕሬዝደንትና የሀንጋሪ መንግስት ተመሳሳይ አቋም ይጋራሉ። መሳሪያ ማጓጓዙንና ጦርነቱን ከማስቀጠል ይልቅ ተኩስ አቁምና የሰላም ንግግር በተቻለ ፍጥነት ያስፈልጋል።"