ፕሬዝደንት ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ከተጋጩ በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ እርዳታ አቋረጡ
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ከኤፒ ጋር በነበራቸው ቆይታ የጦርነቱ ማብቂያ "በጣም፣ በጣም ሩቅ" ብለው መናገራቸው ትራምፕ ተናደው መልስ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የአሜሪካ ኮንግረስ ለዩክሬን የ175 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ እርዳታ ማድረሱን የነንፓርቲዚያን ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል
ፕሬዝደንት ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ከተጋጩ በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ እርዳታ አቋረጡ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ለዩክሬን የሚደገውን ወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጣቸውን ኃይትሀውስ ማስታወቁ ተገልጿል።
ይህ እርምጃ የመጣው ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ ኃይትሀውስ ከገቡ በኋላ አሜሪካ በዩክሬንና ሩሲያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ ከቀየሩና ባለፈው አርብ እለት በኃይትሀውስ ከዘለንስኪ ጋር ኃይለቃል ከተለዋወጡ በኋላ ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ አሜሪካ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ላደረገችው ድጋፍ በቂ ምስጋና አላደረጉም ሲሉ ዘለንስኪን ትችተዋቸዋል።
"ፕሬዝደንቱ ትኩረታቸውን ሰላም መሆኑን ግልጽ አድርገዋል። አጋሮቻችንም ለዚህ አላማ ቁርጠኛ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። እርዳታችን ለመፍትሄው አስተዋጵኦ ማበርከቱን ለማረጋገጥ አቋርጠን እየገመገምን ነው" ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኃይትሀውስ ባለስልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህ ጉዳይ የፕሬዝደንት ዘለንስኪ ቢሮም ሆነ በአሜሪካ የሚገኘው የዩክሬን ኢምባሲ ያለው ነገር አለመኖሩን ዘገባው ጠቅሷል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ከኤፒ ጋር በነበራቸው ቆይታ የጦርነቱ ማብቂያ "በጣም፣ በጣም ሩቅ" ብለው መናገራቸው ትራምፕ ተናደው መልስ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።
"ይህ ዘለንስኪ ያወጣው መጥፎ መግለጫ ነው። አሜሪካ ከዚህ ጋር አትቀጥልም" ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያቸው አስታውቀዋል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የአሜሪካ ኮንግረስ ለዩክሬን የ175 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ እርዳታ ማድረሱን የነንፓርቲዚያን ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።