የትራምፕ አስተዳደር እና ደጋፊዎች ዘለንስኪ ከስልጣን እንዲለቁ ግፊት እያደረጉ እንደሚገኙ ተነገረ
የፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ “ዩክሬን ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ መሪ ያስፈልጋታል” ማለታቸው ተሰምቷል

ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው “እኔን መተካት ቀላል አይደለም” ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እና ደጋፊዎች ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዘለንስኪ አካሄዳቸውን እንዲለውጡ ካልሆነ ከስልጣን እንዲነሱ ግፊት እያደረጉ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
ባለፈው ሳምንት በትራምፕ እና ዘለንስኪ መካከል ከተደረገው ሀይለ ቃል የተሞላበት ውይይት በኋላ የሪፐብሊካን ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘለንስኪን በጦርነቱ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲቀይሩ ወይም ሀላፊነታቸውን እንዲለቁ ግፊት ላይ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ “ዘለንስኪ ጦርነቱን ለማቆም ለመደራደር ዝግጁ ስለመሆናቸው ለአስተዳደሩ ግልፅ አይደለም” ብለዋል።
አማካሪው የትራምፕ ግብ በሞስኮ እና በኪቭ መካከል የግዛት ስምምነትን በማካተት በአውሮፓ የሚመራ የደህንነት ዋስትናን በመተካት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ትራምፕ ዘለንስኪ ከስልጣን እንዲለቁ ይፈልጉ እንደሆን በሲኤንኤን የተጠየቁት ዋልትዝ “ከእኛ ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ የሆነ በመጨረሻም ከሩስያ ጋር በመስማማት ጦርነቱን ማስቆም የሚፈልግ መሪ እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አማካሪው አክለውም “ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከግላዊ ፍላጎት አልያም ፖለቲካዊ ጥቅምን ከማሳካት ተነሳሽነት ጦርነቱን ለማስቆም ከሚደረገው ሂደት ጋር የተለየ ሀሳብ የሚያንጸባርቁ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው” ብለዋል፡፡
የትራምፕ ከፍተኛ አጋር እና የደቡብ ካሮላይና ሴናተር ሊንሴይ ግራሃም አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት የኋይት ሀውስ ግጭትን ተከትሎ ከዚህ በኋላ ጦርነቱን ለማስቆም የትራምፕ አስተዳደር ከዘለንስኪ ጋር በትብብር ስለመስራቱ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ማይክ ጆንሰን እሁድ ዕለት ከኤንቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አፈጉባኤው “አንድ ነገር መለወጥ አለበት ዘለንስኪ ወይ ወደ ቀልቡ ተመልሶ በአመስጋኝነት ወደ ጠረጴዛው ሊመለስ ይገባል ወይም ሌላ ሰው ሀገሪቱን መምራት አለበት” ነው ያሉት ።
ከአሜሪካ ጋር በሚገኙበት ውዝግብ ከፍተኛ ወጥረት ውስጥ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም ለዩክሬን ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ከስልጣናቸው ለመነሳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በለንደን በነበራቸው ቆይታ እሳቸውን የሚተካ መሪ ማግኘት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ መሪዎች እሁድ እለት በለንደን በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለዘለንስኪ ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ ያሳዩ ሲሆን፤ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር አጋሮቻቸው የመከላከያ እገዛቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡