
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብሪታንያን እንዲጎበኙ ከንጉስ ቻርልስ ሶስተኛ የተደረገላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል
ዶናልድ ትራምፕ ብሪታንያን እንዳይጎበኙ የተቃውሞ ፊርማ ዘመቻ ተጀመረ፡፡
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታንመር ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ዋሸንግተን አቅንተው ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ውይይት አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብሪታንያን እንዲጎበኙ ከሀገሪቱ ንጉስ ቻርልስ ሶስተኛ የተላከላቸውን የጉብኝት ግብዣ አስረክበዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕም የንጉስ ቻርልስን ግብዣ መቀበላቸውን የገለጹ ሲሆን ባሳለፍነው አርብ ከዩክሬኑ አቻቸው ዘለንስኪ ጋር በነጩ ቤተ መንግስት ያደረጉት ውይይት ወደ አለመግባባት ከተቀየረ በኋላ ብሪታንያዊያን ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዩክሬናዊንን ክደዋል፣ ለሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በግልጽ ድጋፍ አሳይተዋል በሚል ወደ ሀገራችን እንዳይመጣ የሚል ዘመቻ ጀምረዋል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ብሪታንያ ጉብኝት ግብዣ ይሰረዝ በሚል በበይነ መረብ አማካኝነት እየተካሄደ ያለው ይህ የተቃውሞ ፊርማ እስካሁን ከ70 ሺህ በላይ ዜጎች ፈርመውታልሲል ዴይሊ ኤክስፕረስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የተቃውሞ ዘመቻ አስተባባሪ ከሆኑት መካከል ዞ ጋርድነር በግል የቲክቶክ አካውንቷ ላይ እንዳለችው የተቃውሞ ፊርማውን ብዙዎች እየፈረሙ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፣ ዩክሬናዊን ለሀገራቸው ነጻነት እየከፈሉት ያለውን መስዋዕትነት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አልተረዳም፣ ዩክሬናዊያን ተክደዋል ብላለች፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ብሪታንያን እንዲጎበኙ የቀረበላቸው ግብዣ እንዲሰረዝ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ሊከራከርበት እና ሊወያይበት እንደሚገባም እየተጠየቀ ይገኛል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዩክሬን በተጨማሪ ሌላኛዋን እና በንጉስ ቻርልስ ሶስተኛ የበላይነት በምትመራው ካናዳ ለይም ክህደት ፈጽሟል፣ ግብዣው ሊሰረዝ እንደሚገባም ተጠይቋል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 ላይ ዶናልድ ትራምፕ ብሪታንያን እንዳይጎበኙ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች የተቃውሞ ፊርማ ቢፈርሙም ጉብኝቱን ማስቀረት አልቻሉም ነበር፡፡