በአፍሪካ ቀንድ ከ37 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ኬንያ ለረሃብ ከታጋለጡ ሀገራት ይገኙበታል
ድርጅቱ “ያለው የምግብ ችግር ወደ ጤና ቀውስ እንዳይለወጥ ለመከላከል 123 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል” ብሏል
በአፍሪካ ቀንድ ከ37 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
ከእነዚህ መካከል ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት መሆናቸውም ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ያጋጠመው ረሃብ ባለፉት 70 ዓመታት ካጋጠሙ የረሃብ አደጋዎች አስከፊ የሚባል ነውም ብሏል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣ የምግብ ዋጋ ንረት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተከሰተው ድርቅ አስከፊ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳበረከቱም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ድርጅቱ፤ ለረሃብ የተጋለጡትን ሰዎችን ህይወት ለመታደግም ሆነ በረሀብ ምክንያት ሊከሰት ከሚችል በሽታ ለመከላከል ጠንካራ የጤና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ሲል ጠይቋል።
እየጨመረ ለመጣው የጤና ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት እና የምግብ ችግር ወደ ጤና ቀውስ እንዳይለወጥ ለመከላከል 123 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አስታውቋል የዓለም ጤና ድርጅት።
የዓለም ጤና ድርጅት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ረዳት ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂማ ሶስ ፎል “ሁኔታው አስከፊ ሆኗል፣ እናም አሁን እርምጃ መውሰድ አለብን”፤በዚህ የገንዘብ እጥረት ውስጥ መቀጠል አንችልም ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአደጋ ቁጥጥር ስራ አስኪያጅ ሶፊ ማይስ በበኩላቸው "ላለፉት አራት ወቅቶች ዝናብ ይገኛል ተብሎ ቢተነበይም አልዘነበም፤ በአምስተኛው ወቅትም ቢሆን ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ድርቅ ባለባቸው ቦታዎች ችግሩ እየተባባሰ ሄዷል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለረሃብ ከታጋለጡ ሀገራት ይገኙበታል።
በምሰራቅ አፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
በቀጠናው ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መከሰቱን የገለጹት ዋና ጸሃፊው፤ በዚህም በቀጠናው የምግብ ዋስትና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተናገርዋል፡፡
“አሁን ላይ በቀጣናው 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና ያስፈልጋቸዋል”ም ነበር ያሉት ዋና ጸሃፊው፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ “የቀጣናው ሀገራት በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ ተለዋዋጭ ተጽእኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ማሳሰባቸውም የሚታወስ ነው።