የዓለም ጤና ድርጅት ‘የዝንጀሮ ፈንጣጣ’ የሚለውን ስያሜ 'ኤምፖክስ' በሚል መቀየሩን ገለጸ
‘የዝንጀሮ ፈንጣጣ’ በሽታ መጠሪያ ዘረኝነት እና መገለል በማስከተሉ የበሽታውን ስያሜ ‘ኤምፖክስ’ እንዲሆን ድርጅቱ ወስኗል
ሁለቱም ስሞች በጋራ ለአንድ ዓመት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን ዋናው ቃል ሲቋረጥ አዲሱ መጠሪያ ይቀጥላል ተብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት ‘የዝንጀሮ ፈንጣጣ’ በሽታ መጠሪያ ዘረኝነት እና መገለል ያስከትላል በሚል ቅሬታ የበሽታውን ስያሜ "ኤምፖክስ" በሚል መተካቱን ተናግሯል።
አዲስ የተመረጠውን ቃል መጠቀም እንደሚጀምር እና ሌሎች ተቋማትም ይህንን እንዲከተሉ አሳስቧል።
አሁን ላይ ሁለቱም ስሞች ለአንድ ዓመት ያህል በአንድ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆኑን የተናገረው ድርጅቱ፤ ‘የዝንጀሮ ፈንጣጣ’ ሲወገድ ‘ኤምፖክስ’ ሙሉ ለሙሉ ይተካል ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ‘የኤምፖክስ’ ስርጭት ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ መሆኑን ካወጀ ብዙም ሳይቆይ የሽታውን ስያሜ ስለመቀየር የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎችን ማማከሩን ተነግሯል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሲስፋፋ በአንዳንድ ማህበረሰቦች ላይ ዘረኝነት እና ማጥላላት መስተዋሉን ሪፖርት ተደርጎልኛልም ብሏል።
በፈረንጆቹ በ1958 የተገኘውና የበሽታ ምልክቶች በታየበት የመጀመሪያው እንስሳ የተሰየመው "ኤምፖክስ" በዚህ ዓመት በአብዛኛው በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ባሉ ሀገራት ውስጥ ተሰራጭቷል።
አሁን 110 ሀገራት 80 ሽህ የሚያህሉ የተረጋገጡ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ 55 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ተመራማሪዎች “ኤምፖክስ’ በቤልጂየም እና በስፔን በኩል ከተሰራጨ በኋላ በምዕራባውያን ገገሮች ወረርሽኙ እንደቀሰቀሰ ያምናሉ።
በበለጸጉ ሀገራት የክትባት ጥረቶች ከቁጥጥር እርምጃዎች ጋር በሽታው ከወራት በፊት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን ሲቢሲ ዘግቧል።
በአፍሪካ ውስጥ በሽታው በዋነኝነት የሚያጠቃው እንደ አይጥ እና ጊንጥ ካሉ ከተጠቁ እንስሳት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ነውም ተብሏል። ‘ኤምፖክስ’ ጋር የተገናኙት አብዛኛዎቹ ሞቶች በአፍሪካ ውስጥ ናቸው የተባለም ሲሆን፤ ምንም አይነት ክትባት የለም ብለዋል ባለሙያዎቹ፡፡