ሱዳን በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው ማግኘቷን ገለጸች
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመካከለኛውና በምዕራብ አፍሪካ በብዛት ተከስቷል
የዝንጀሮ ፈንጣጣው በአንድ የ 16 ዓመት ተማሪ ላይ መገኘቱን ሱዳን አስታውቃለች
በሱዳን በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው መገኘቱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመካከለኛውና በምዕራብ አፍሪካ በብዛት የተከሰተ ሲሆን አሁን ደግሞ በሱዳን መገኘቱ ተገልጿል።
ሰኔ ላይ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙ እንደተገኘባቸው ተገልጾ ነበር። ሱዳንም በተመሳሳይ በምዕራብ ዳርፉር የዝንጀሮ ፈንጣጣ ያለበት ሰው ማግኘቷን ገልጻለች። የዝንጀሮ ፈንጣጣው በአንድ የ 16 ዓመት ተማሪ ላይ መገኘቱን ነው ሱዳን የገለጸችው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣው በአንድ ተማሪ ላይ መገኘቱ የተረጋገጠው ሃሙስ ዕለት በብሔራዊ የህዝብ ጤና ቤተሙከራ በተካሄደው ምርመራ መሆኑን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ወረርሽኙ ከአንድ ሰው ውጭ በሌሎች ላይ አለመገኘቱንም ነው ሱዳን ያስታወቀችው።
ወረርሽኙ አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩት 38 ሰዎች ቢሆኑም በሽታው የተገኘው ግን በአንድ ሰው ላይ ብቻ ነውም ተብሏል።
የዳርፉር ግዛትና የሱዳን የጤና ሚኒስቴር ጉዳዩን እየተከታተሉት እንደሆነ ገልጸዋል ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚኖር የቅርብ ንክኪ ሊተላለፍ የሚችል ነው። ቫይረሱ በቆሰለ ቆዳ፣ በመራቢያ አካል ወይም በዐይን፣ በአፍንጫ እና በአፍ አማካኝነት ወደ ሰውነት ሊገባ የሚችል ነው።
የዝንጆሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከ60 ሀገራት ላይ ተከስቶ ሶስት ሞት ተመዝግቧል።
በኢትዮጵያ እስካሁን በላብራቶሪ የተረጋገጠ የዝንጆሮ ፈንጣጣ ታማሚ ያልተመዘገበ ሲሆን የበሽታው ቅኝት እና የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።