ይህ ሀይል በርካታ የሱዳን ጦር ካምፕን በመቆጣጠር ላይ እንደሆነ ተገልጿል
የሱዳን አርኤስኤፍ ሀይል ማን ነው?
በሱዳን ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ጡረታ ወጥተው የነበሩ የቀድሞ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር አባላት ወደ ስራ መመለሳቸው ተገልጿል።
በሱዳን ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ በብሔራዊ ጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።
እስካሁን ንጹሀንን ጨምሮ በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ሲገለጽ ብሄራዊ ቴሌቪዥን፣ ኤርፖርት እና የጦር ካምፖችን ለመቆጣጠር ውጊያ እየተካሄደ ነው ተብሏል።
ለመሆኑ ይህ ከሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር ጋር እየተዋጋ ያለው ፈጥኖ ደራሽ ማን ነው? እንዴት ተመሰረተ? በማንስ ይመራል? ለምንስ ተመሰረት እሚለውን እንደሚከተለው እንዳስሳለን።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ወይም አርሴኤፍ በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄመቲ ይመራል።
ይህ ሀይል በዳርፉር በፈረንጆቹ 2013 የተከሰተውን የጎሳ ግጭት ለማስቆም በሚል ነበር የተቋቋመው።
የዳርፉር ጎሳ ግጭት ቀስ በቀስ ቢቆምም ከዚያ በኋላ በሱዳን እና ከሱዳን ውጪ ባሉ ጦርነቶች ተሳትፏል።
ለአብነትም የዚህ ሀይል አባል የሆኑ 40 ሺህ ወታደሮች በ2015 ሳውዲ አረቢያ በሚመራው የየመን ጦርነት ተሳትፏል።
እንዲሁም በሊቢያ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ ሲሆን በወጣቶች የተገነባ መሆኑ አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በ2019 ከስልጣን ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ ከዳርፉር ውጪ ባሉ የሀገሪቱ ስፍራዎች በጸጥታ ማስከበር ስራ ላይ ሲሰማራ ቆይቷል።
ተጽዕኖውን ተከትሎም በስልጣን ላይ ባለው የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ላይ የምክትልነት ሀላፊነትን አግኝቷል።
ይሁንና ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳድር እንድትመለስ ውይይት መጀመሩን ተከትሎ ወታደራዊ መንግሥቱ ስልጣኑን እንዲያስረክብ ስምምነት ላይ ይደረሳል።
ይሁንና ይህ ሀይል ወደ ሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር እንዲካተት ውሳኔ ላይ ቢደረስም መቼ ይዋሀድ እሚለው ጉዳይ ለግጭት መዳረጉ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም አሁን በይፋ ከብሔራዊ ጦሩ ጋር ወደ ጦርነት ያመራ ሲሆን የጦር ካምፖችን፣ ኤርፖርት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመቆጣጠር ላይ ነው ተብሏል።