የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ቤተመንግስቱንና የካርቱም ኤርፖርትን መያዙን ገለጸ
አሜሪካ እና ሩሲያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በሱዳን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ ነው
በሱዳን በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል ያለው አለመግባባት ሀገሪቱን ከባድ ውጥረት ውስጥ ከቷታል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አር ኤስ ኤፍ) ቤተመንግስቱን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
ቤተመንግስቱ የሱዳን ጦር መሪው መኖሪያ እንደነበር ተገልጿል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ የካርቱም ኤርፖርትንም መያዙን መግለጹን ሬውተርስ ን ዘግቧል።
ቡድኑ በሜሮዬ እና ኤል ኦቤድ የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችንም መቆጣጠሩን ማሳወቁ ነው እየተነገረ ያለው።'
በሱዳን መዲና ካርቱምና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የተቀሰቀሰው ግጭት አሳሳቢ መሆኑን አሜሪካ እና ሩሲያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እየገለጹ ነው።
በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ እና በሀገሪቱ ጦር መካከል የሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉን ሬውተርስ ዘግቧል።
በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሀገሬኡ ጦር የካርቱምም ሆነ ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያ "ታጣቂ" ሲል በገለጻቸው ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች አለመያዛቸውንና ዋናዋና ተቋማትም ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳልሆኑ ነው የገለጸው።
እየወጡ ያሉ ምስሎች ግን የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ከባድ ውጥረት ውስጥ መሆኑንና መንገደኞችም ሲንገላቱ ያሳያሉ።
ከሳኡዲ የተነሳ አውሮፕላንም በካርቱም ያለው ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ወደመጣበት ተመልሷል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
የሱዳን አየር ሃይል በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑንም ተገልጿል።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ተኩስ አስቀድሞ በመክፈት እርስ በርስ እየተወቃቀሱ ሲሆን፥ ንጹሃን ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ከካርቱም የሚወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል።
በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አር ኤስ ኤፍ) በበኩሉ በዛሬው እለት በካርቱም የሚገኘው ወታደራዊ ጣቢያው በሱዳን ጦር ተከቦ ተኩስ እንደተከፈተበት ገልጿል።
ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ “የከፋ ጥቃት” ነው ያለውን የሱዳን ጦር ድርጊት ሁሉም ሱዳናዊ እንዲያወግዘው ጠይቋል።
ለሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ አደራዳሪዎችም ጉዳዩን እንደሚያሳውቅ ነው ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
የሱዳን ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለቱም ሀይላት ውጥረቱን እንዲያረግቡ ጠይቀዋል።
በሱዳን የሲቪል አስተዳድር ለመመስረት ውይይቶች ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ወደ ብሔራዊ ጦሩ የሚዋሀድበት ጊዜ ላይ ስምምነት መፍጠር አልተቻለም።
ከሰሞኑ የሀገሪቱ መከላከያ ቃል አቀባይ ሱዳን በታሪካዊ እጥፋት ላይ እንደምትገኝ ገልጾ ካርቱም ዲሞክራሲያዊት አልያም ወደ ለየለት እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ባለፈው ሀሙስ በሜሮዌ ከተማ ያደረገው እንቅስቃሴ ለውጥረቱ መነሻ መሆኑ አይዘነጋም።
የአር ኤስ ኤፍ ሃይሎች በካርቱምና በሌሎች ከተሞች ያደረጉት እንቅስቃሴ ከእውቅናዬ ውጭ ነው ያለው የሱዳን ጦር ግጭት እንዳይቀሰቀስ ሲያሳስብ ነበር።
የሱዳን ጦርና የሄሜቲ ሃይሎችን አለመግባባት ውስጥ የከተተው ጉዳይ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ወደ መደበኛ ሰራዊቱ የሚቀላቀሉበት የጊዜ ገደብ እንደሆነ ተነግሯል።
በሄሜቲ የሚመራውና ከ100 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በ2019 ኦማር ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን በማስወገዱ ሂደት ከጀነራል አብደልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በጥምረት መንቀሳቀሱ ይታወሳል።
በዳርፉር ተፈሪ የነበሩት የሚሊሻ አዛዡ ጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ ነው።