የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይልን ወደ መከላከያ ሰራዊት የማዋሃዱ ስራ ዋነኛ የፖለቲካ ልዩነት ሆኗል
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በሀይል ከስልጣን ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ በጎረቤት ሀገር ሱዳን አለ መረጋጋት ሰፍኗል፡፡
የቀድሞው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ዶክተር አብደላ ሀምዶክ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን ተከትሎ ብዙዎች ሱዳን ወደ መረጋጋት መምጣቷን አምነውም ነበር፡፡
ይሁንና በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን መንግስት በሀይል ማፍረሱን ተከትሎ በሱዳን ዳግም የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊፈጠር ችሏል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክብ ህዝባዊ ተቃውሞ በመበራከታቸው ምክንያት በዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች አማካኝነት ፖለቲከኞች ወደ ድርድር ተቀመጡ፡፡
ታዛቢዎች በተገኙበት ሲካሄድ የቆየው ይህ ድርድርም ወደ ስምምነት መምጣቱ ሲገለጽ ባሳለፍነው ሳምንት የስምምነት ፊርማ ከተፈረመ በኋላ በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ሚያዚያ 11 ቀን 2023 ደግሞ የሲቪል አስተዳድር ይቋቋማል ተብሎም ነበር፡፡
ይሁንና ይካሄዳል የተባለው የመንግስት ምስረታ ስምምነት በተደጋጋሚ የተራዘመ ሲሆን ለመራዘሙ ምክንያት ደግሞ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ወደ ሀገሪቱ ብሄራዊ ጦር በሚቀላቀልበት ጊዜ ላይ መስማማት ባለመቻሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አለመግባባቱን ተከትሎ በሱዳን ከፍተኛ አለመረጋጋት የተከሰተ ሲሆን ሱዳን በታሪካዊ እጥፋት አደጋ መካከል ላይ መሆኗን የሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ናቢል አብዱላህ ተናግረዋል፡፡
የሱዳን ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ አመራሮች በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ወደ ሀገሪቱ ብሄራዊ ጦር እንዲዋሃድ ቢስማሙም በሚዋሃድበት ጊዜ ላይ ግን አለመስማማታቸው ተገልጿል፡፡
የፈጥኖ ደራሹ ተወካዮች በ10 ዓመት ውስጥ ውህደቱ ይፈጸም ሲሉ ፖለቲከኞች በሁለት ዓመት ፤ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ደግሞ በአምስት ዓመት ውስጥ እንዲፈጸም ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡
ይህን ተከትሎ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አባላት በሱዳን የከፋ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል በማስጠንቀቅ ላይ ሲሆኑ የሀገሪቱ ጦር በበኩሉ ሱዳን አስከፊ ቀውስ እና መልካም የዴሞክራሲ እድል መካከል ላይ መሆኗን አስጠንቅቋል፡፡