የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብዳቤ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የህግ ስህተት እንዳለበት የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል
የፌደራል መንግስት ወደ አማራ ክልል ጣልቃ እንዲገባ የመጠየቅ ህጋዊ ስልጣን ያለው ማን ነው?
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በትናንትናው ዕለት በክልሉ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በመደበኛው የጸጥታ መዋቅር ማስከበር በሚቻልበት አቋም ላይ አለመሆኑን በመጥቀስ የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የርዕሰ መስተዳድሩን ጥያቄ መነሻ በማድረግም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ማስተላለፉን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክርቤት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጉዳይ አለመወያየቱን እና አለማጽደቁን የምክርቤት አባላት ለአል ዐይን ተናግረዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብዳቤ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የህግ ስህተት እንዳለበት የህግ ባለሙያዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የህግ ባለሙያው ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ በክልሉ በሚደረጉ አበይት ክስተቶች ላይ የመወሰን ስልጣን ያለው የክልሉ ምክር ቤት እንጂ ርዕሰ መስተዳድሩ አይደሉም ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር ሳይመክሩ እና ውሳኔ ሳያሳልፍ የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅድ ደብዳቤን መጻፋቸው ስህተት መሆኑንም ጠበቃው ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የመፍቀድ ስልጣን የክልሉ ምክር ቤት ሆኖ ሳለ ምክር ቤቱ በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ወደ ጎን በመተው የፌደራል መንግስት ወደ ክልሉ እንዲገባ የሚፈቅድ ደብዳቤ መጻፋቸው መሰረታዊ የህግ ጥሰት እንደሆነም ጠበቃ ሔኖክ አክለዋል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የርዕሰ መስተዳድሩን ደብዳቤ መሰረት በማድረግ የወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትክክል አይደለም የሚሉት ጠበቃ ሔኖክ የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ሳይቀርብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔውን ማሳለፍ አልነበረበትምም ብለዋል፡፡
ጠበቃ ሔኖክ አክለውም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ተገቢውን የሕግ ድጋፍ ሳይዝ ውሳኔ ማስተላለፉ በአስቸኳይ አዋጅ ውሳኔው አተገባበር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በላይ የዜጎችን መሰረታዊ መብት የሚጋፋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለት የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ የጸጥታ ሁኔታው ላይ ሰፊ ጊዜ ወስደው መምከራቸውን እና የመፍትሔ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በዚህ ጉባኤ ላይ በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ወደ ቀድሞ ሰላሙ ለመመለስ የጦር መሳሪያ ያነሱ አካላትን በሽምግልና እና በውይይት እንዲፈታ ከስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡
በተለይም በየዞኑ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተውጣጣ አምስት አባላት ያሉት ቡድን ተዋቅሮ ነፍጥ ያነሱ ዜጎቸን ወደ እርቅ እና ሰላም ለመመለስ ወደ ተግባር ተገብቶ ነበር የሚሉት እነዚህ የምክር ቤት አባላት ይህ የመፍትሔ እቅድ ውጤቱ ሳይገመገም ርእሰ መስተዳድሩ የፌደራል መንግስት ወደ ክልሉ ጣልቃ እንዲገባ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ከብዙሀን መገናኛዎች መስማታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብዳቤ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የህግ ስህተት እንዳለበት የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።