የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ በአማራ ክልል ትንኮሳ እየተፈጸመበት መሆኑን መናገሩ ይታወሳል
የአማራ ክልል የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ጠየቀ።
በአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ በክልሉ ያለው ሁኔታ ከአቅም በላይ ነው ብለዋል።
በክልሉ ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር በይፋ ጥያቄ አቅርበዋል።
በክልሉ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ለማዋል እስካሁን በክልሉና በፌደራል የፀጥታ ሃይሎች በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
ሆኖም በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስና ጥቃት በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በአስቸኳይ ለማስቆም የፌደራል መንግስት ከመደበኛው የህግ ማስከበር ስርአት ባሻገር በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በአፋጣኝ እንዲተገበር መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል።
ክልሉ ወደ ቀደመ መረጋጋቱ እንዲመለስ ዜጎች ሰላማቸው ተመልሶ አርሶአደሩ ወደ እርሻው ክልሉም ወደ ልማት ስራዎች ፊቱን እንዲያዞር ለማድረግ መንግስት ያለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባልም በሚል የፌደራል መንግስት ጥያቄ ቀርቦለታል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በትናንትናው ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል ማለታቸው ይታወሳል።
ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ይኖራሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊና የውይይት አግባብ ነው ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።
ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ፣ ያለንን የሚያሳጣ እና በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ ሲሉም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ “የሀገር ሽማግሌ የጠፋ፣ መካሪ የሃይማኖት አባት የታጣ ይመስል ሁላችንንም የሚያባላና የሚበላ አካሄድ ይስተዋላል”ም ነው ያሉት አቶ ደመቀ።
ይህም “ከውጭና ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል” ሲሉም ማከላቸው ይታወሳል።