የአማራና ትግራይ ክልሎች ከሰሞኑ ከወሰን ጋር ተያይዞ ባወጡት መግለጫ ዙሪያ የፌደራል መንግስት ምን አለ?
የትግራይ ክልል “የአማራ ክልል የትግራይ መሬቶችን በክልሉ ካርታ ላይ በማስፈር እያስተማረበት ይገኛል” ሲል ከሷል
የአማራ ክልል “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን እየገደለና እያሰቃየ ነው” ሲል ከሷል
የፌደራል መንግስት ማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች በህዝበ ውሳኔ ብቻ እንዲፈቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የአማራ ክልል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሮች ከሰሞኑ ከወሰን ጋር ተያይዞ እርስ በእርስ በሚያወጡት መግለጫ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው፤ የአማራ ክልል መንግስት “የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ” በክልሉ ካርታ ላይ አስፍሯል፤ የትግራይ ክልል መሬቶች የሰፈሩበትን ካርታ በትምህርት ካሪኩለሙ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ ተረድቻለሁ” ማለቱ ይታወሳል።
የአማራ ክልል በበኩሉ የአማራ ክልል “የትግራይጊዜያዊ አስተዳደር የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን እየገደለና እያሰቃየ ነው” ሲል የከሰሰ ሲሆን፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራቶቹ እንዲቆጠብም አስተንቅቋል።
- የትግራይ ክልል “የአማራ ክልል የትግራይ መሬቶችን በክልሉ ካርታ ላይ በማስፈር እያስተማረበት ይገኛል” ሲል ከሰሰ
- የአማራ ክልል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራቶቹ እንዲቆጠብ አስጠነቀቀ
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ “ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌላውና የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው” ብለዋል
“ከወሰን ጋር ተያይዝው የሚነሱ ጥያቄዎችና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በድርደር ከመፍታት ይልቅ ወሰንን በኃይል እናስከብራለን የሚል አካሄድ ካለፈው ስህተት አለመማርን ያመለክታል” ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።
“ትግራይን በተመለከተ የፌደራል መንግስት አቋም የማይናወጥ ነው” ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ “የፌደራል መንግስት ምንም የሚቀያይረው ነገር የለም፤ ነገሩን የቀያየረው አካል መልሶ ከሳሽ መሆን አይችልም” ሲሉም ተናግረዋል።
“የፌደራል መንግስት ማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች በህበ ውሳኔ ብቻ እንዲፈቱ አቅጣጫ አስቀምጧል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ከዚህ በኋላ በተቀመጠው አቅጣጫ ብቻ ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል፤ ከዚህ ውጪ ያሉ አካሄዶች ለጊዜው ትፍር የሚያስገኙ ቢመስሉም ዘላቂነት የላቸውም” ብለዋል።
ይህንን ተሳቢ በማድረግ በፌደራል እና ከሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የወሰንና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ የፈረደራል መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን በማሰማራት የአካባቢውን ደህነንተ የማስከበርና የመቆጣጠር ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ተፈናቃዮችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ መኖሪያ ቀኤያቸው እንደሚለሱ እንዲደረግ፣ ህዝቡ ምርጫ አድርጎ የአካባቢው አስተዳደሮች እንዲመሰረቱ እና ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ የአካባቢው ህዝቦች በተረጋጋ መንፈስ ህዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂዱም ገልጸዋል።
ሁለቱ ክልሎች በመግለጫ እር በእርስ ከመወቀቃቀስ ይልቅ በአብይ ኮሚቴ ታግዘው በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻቸውን መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።