የአንድ ወንድ ልጅ ወላጅ የሆኑት ጥንዶቹ በጀርባ ህመም እና በመርሳት በሽታ ለዓመታት ሲሰቃዩ ነበር ተብሏል
እስከ መቃብር የጸናው ፍቅር
ጃን እና ኤልስ የተሰኙት ባልና ሚስት ሆላንዳዊያን ሲሆኑ ከልጅነታቸው ጀምሮ አብረው ያደጉ ናቸው፡፡
ከመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤት የጀመረው የሁለቱ ጥንዶች ወዳጅነት ወደ ፍቅር ተቀይሮ ከ50 ዓመት በላይ በትዳር ኖረዋል፡፡
በሰሜናዊ ሆላንድ በምትገኘውፍራይስ ላንድ ተብላ በምትጠራው የባህር ዳርቻ ህይወታቸውን መርተዋል፡፡
ጃን ሀገሩ ሆላንድን በበረዶ መንሸራተት ውድድሮች ላይ ወክሎ ከተጫወተ በኋላ በዚሁ ሙያ አሰልጣኝ ሆኖ ሲያገለግል ኤልስ ደግሞ እድሜ ልኳን በማስተማር ሙያ ተሰማርታለች፡፡
የ70 እና 71 ዓመት እድሜ ያላቸው እነዚህ ጥንዶች የአንድ ወንድ ልጅ ወላጅ ሲሆኑ የልጅ ልጅም ማየት ችለዋል፡፡
ጥንዶቹ አብዛኛው ህይወታቸውን በባህር ላይ በተሰራ መኖሪያ ቤት የኖሩ ሲሆን በሂደት ያጋጠማቸው ህመም ግን ህይወታቸውን አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል፡፡
በተለይም ባልየው ጃን በጀርባ ህመም ለዓመታት ህመምተኛ የሆነ ሲሆን ከ10 ዓመት በፊት የቀዶ ህክምና ቢያደርግም ህመሙ ሊቆምለት አልቻለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ71 ዓመቷ ኤልስም በመርሳት በሽታ ስትሰቃይ ነበር የተባለ ሲሆን ከ20 ቀን በፊት በሐኪሞች ታግዘው ከስቃይ እንዲያርፉ እና ህይወታቸውም እንዲያልፍ ተደርጓል ተብሏል፡፡
በሆላንድ አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ በማይድን ህመም ከተያዘ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሞት መሞት የሚፈቅድ ህግ አለ፡፡
በዚህ ህግ መሰረትም ታማሚዎች አልያም የታማሚ ቤተሰቦች በሚወስኑት ውሳኔ እና በሐኪሞች ምክረ ሀሳብ አማካኝነት ህይወታቸው እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡
ለዓብነትም በ2023 ዓመት ከ9 ሺህ በላይ ሆላንዳዊያን በበማይድን ህመም ምክንያት ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች በሐኪሞች ታግዘው ህይወታቸው እንዲያልፍ እንደተደረገ በዘገባው ለይ ተጠቅሷል፡፡