አሜሪካዊያን ከኤሌክትሪክ መኪኖች ፊታቸውን ለምን አዞሩ?
በቅርቡ የተሰራ ጥናት አሜሪካዊያን በኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ ያላቸው ፍላጎት መቀነሱን አመላክቷል
የሀገሪቱ መንግስት እስከ 2032 የአዳዲስ ኤሌክትሪክ መኪኖች ሽያጭ ድርሻ 56 በመቶ እንዲሆን ወጥኗል
ዘመን አመጣሾቹ የኤሌክትሪክ መኪኖች ተቀባይነት በአሜሪካ ቅናሽ እያሳየ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የጆ ባይደን አስተዳደር ከአከባቢ ጥበቃ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የኤሌክትሪክ መኪኖች ወደ ገበያው በሰፊው እንዲገቡ እያደረገ ቢሆንም፣ ተቀባይነታቸው ከግዜ ወደጊዜ እያሽለቆለቆለ እንደሚገኝ ነው ፋይናንሻል ታይምስ የዘገበው፡፡
ሆኖም አሁንም አሜሪካ ከቻይና እና ከአውሮፓ ቀጥሎ ከፍተኛዋ የኤሌክትሪክ መኪኖች መዳረሻ ሀገር ናት። በ202፣ 1.6 ሚሊየን አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሸርካሪዎች በመላው አሜሪካ ተሸጠዋል፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ አሜሪካዊን ለምን የኤሌክትሪክ መኪኖችን መግዛት አቆሙ በሚል ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት፡፡
46 በመቶዎቹ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመግዛት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። 13 በመቶዎቹ ደግሞ ተሸከርካሪዎቹን የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ወይም ከቤተሰባቸው አባል አንዱ የተሸከርካሪዎቹ ተጠቃሚ እንደሆነ ነው ምላሽ የሰጡት፣ 9 በመቶዎቹ ደግሞ የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ ጉልበትን የሚጠቀም (ሀይብሪድ) ተሸከርካሪዎች ምርጫቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን በመጡበት አመት ትኩረት ካደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል የነዳጅ ተሸከርካሪዎችን የገበያ ድርሻ መቀነስ ነበር፡፡ የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ኤጄንሲ በ2032 የአዳዲስ ኤሌክትሪክ መኪኖችን ሽያጭ ድርሻን 56 በመቶ ለማደረስ አቅዷል፡፡
ሆኖም አሜሪካዊያን ዜጎች ቀዝቃዛ የአየር ንብረት በሚኖርበት ወቅት የመኪናዎቹ ባትሪ ላይ የሚኖረው ኬሚካል ሪአክሽን የመኪኖቹ ጉልበት እንዲቀነስ እያደረገው ነው በሚል እያማረሩ ነው፡፡
በተጨማሪም የሀይል መሙያ ጣቢያ መሰረተ ልማቶች አናሳነት እና ሀይል ለመሙላት የሚወስዱት ጊዜ መርዘም እንዲሁም መኪኖቹ በአንድ ጊዜ ቻርጅ የሚሄዱት ርቀት አነስተኛ መሆን አሜሪካኖች ተሸከርካሪዎቹን እንዳይገዙ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በሌላ በኩል ተሸከርካሪዎቹ የሚሸጡበት ዋጋ ከፍተኛነት ሌላው ዋነኛ ምክንያት ነው። በተያዘው አመት የካቲት ወር ላይ በአሜሪካ ገበያ አማካኝ የአዲስ የኤሌክትሪክ መኪና መሸጫ ዋጋ 52 ሺ ዶላር ሲሆን የኤሌክትሪክ መኪኖች ደግሞ እስከ 47 ሺህ ዶላር ድረስ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል፡፡
የዋጋው ሁኔታ ከግዜ ወደጊዜ ቅናሽ እያሳየ ቢገኝም የተሸርካሪዎቹ ቴክኖሎጂዎች አሁንም የነዳጅ መኪኖችን ያህል ተመራጭ እንደማያደርጋቸው ፋይናንሻል ታይምስ ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት ውጤት አመላክቷል፡፡
ከ20 እስከ 40ዎቹ አድሜ ውስጥ የሚገኙ አሜሪካዊያን የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ሲኖራቸው 45 አመት እና ከዛ በላይ የሆኑ አሜሪካዊያን ደግሞ፤መኪኖቹን ልጆችን ትምህርት ቤት ለማድረስ ወደ ገበያ ስፍራዎች ለመጓዝ ካልሆነ በቀር ራቅ ወዳሉ ስፍራዎች ይዘዋቸው ለመጓዝ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል፡፡
እንደ አለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጄንሲ መረጃ ከሆነ ደግሞ የኤሌክትሪክ መኪኖች አለም አቀፋዊ ተቀባይነት እያደገ መጥቷል። በ2024 የተሸከርካሪዎቹ ሽያጭ እስከ 17 ሚሊየን ሊደርስ እንደሚችል ነው ትንበያውን ያስቀመጠው፡፡
በአለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ሽያጭ ቻይና 60 በመቶው ድርሻ ሲኖራት አውሮፓ 25 በመቶ አሜሪካ 10 በመቶ ድርሻን ይዘዋል፡፡