አፕል የኤሌክትሪክ መኪና ለመስራት የጀመረውን ፕሮጀክት ማቋረጡ ተነገረ
ኩባንያው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ነው ተብሏል
አፕል እጅግ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪውን በ2024 አልያም 2025 በይፋ እንደሚያስተዋውቅ ይጠበቅ ነበር
አፕል የኤሌክትሪክ መኪና ፕሮጀክቱን ማቋረጡ ተገልጿል።
ኩባንያው በይፋ እስካሁን ባያሳውቅም ከአስር አመት በፊት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት አዲስ ፕሮጀክት መጀመሩ ሲነገር ቆይቷል።
የአይፎን አምራቹ ኩባንያ የኤሌክትሪክ መኪናውን በዚህ አመት ወይም በቀጣዩ አመት በይፋ ያስተዋውቀዋል ሲባል ቢቆይም ፕሮጀክቱን መሰረዙን ብሎምበርግ አስነብቧል።
ሬውተርስም ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው አፕል ለአስር አመት ቢሊየን ዶላሮችን ያወጣበትን ፕሮጀክት አቋርጧል።
በፕሮጀክቱ ላይ ይሳተፉ የነበሩ ከሁለት ሺህ በላይ ሰራተኞችም ወደ ኩባንያው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ክፍል ይዛወራሉ መባሉ ነው የተዘገበው።
አፕል ስለፕሮጀክቱ መቋረጥ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ተንታኞች ግን ኩባንያው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፕሮጀክቱን ማቋረጡን እንደ መፍትሄ ወስዶት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
በስማርት ስልኮቹ ዘመናዊነት ቀዳሚ የነበረው አፕል በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ግን ከአልፋቤት እና ማይክሮሶፍት አንጻር እጅግ ወደኋላ መቅረቱንም ይጠቅሳሉ።
ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ይልቅ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ መስራት አዋጭ መሆኑን በመረዳት ፕሮጀክቱን መሰረዙም “ትክክለኛ እና ሲጠበቅ የነበረ ውሳኔ ነው” ይላሉ የኮንስትሌሽን ሪሰርች ዋና ስራ አስፈጻሚ ሬይ ዋንግ።
ሌላኛው የቴክኖሎጂ የጥናት ተቋም ካውንተርፖይንትም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተገጠመላቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ሽያጭ እያደገ መሄዱን ይጠቁማል።
በ2024 100 ሚሊየን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጠቀሙ ስማርት ስልኮች ለሽያጭ እንደሚቀርቡና በ2027 ይህ አሃዝ ወደ 500 ሚሊየን ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም በመጥቀስ።
በአንጻሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በገበያው ያላቸው ተፈላጊነት ባለፉት ወራት መቀዛቀዝ እያሳየ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካዎቹ ፎርድ እና ጀነራል ሞተርስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ምርቶችን ለማሳደግ የያዙትን እቅድ ያራዘሙ ሲሆን፥ ሪቪያን የተሰኘው መኪና አምራችም ከሰራተኞቹ ውስጥ 10 በመቶውን ለመቀነስ ወስኗል።
የኤለን መስኩ ቴስላም ከቻይናው ቢዋይዲ የገጠመውን ፉክክር ተከትሎ በቻይና እና አውሮፓ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ ተገዷል።
አፕልም በዚህ ፈታኝ ፉክክር ባለበት ገበያ ውስጥ ከመግባት ይልቅ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ለማተኮር በማሰብ የ10 አመት ፕሮጀክቱን እንዳቆመ እየተነገረ ነው።