የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራ በረራውን እንዲያቆም ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ አስመራና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ሲያደርግ የነበረውን በረራ “አቋርጫለሁ” ብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ “አስመራ ውስጥ ያለንን ገንዘብ እንዳናወጣ ተከልክለናል” በሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ሲያደርግ የነበረውን በረራ አቋርጫለሁ ብሏል።
ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ያለው አየር መንገዱ በኤርትራ ያለው አሰራር አስቸጋሪ እና ከቁጥጥሩ ውጪ መሆኑ ለበረራው መቋረጥ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አየር መንገዱ በረራውን ከዛሬ ጀምሮ ማቋረጡን ገልፀዋል።
አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በኤርትራ ውስጥ አገልግሎቱን ለመስጠት ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ የአሰራር ችግር ምክንያት እንደሆነም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።
ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው አክለውም፤ ምክንያቱን ባላወቅነው መንገድ አስመራ ውስጥ ያለንን የዶላር ገንዘብ እንዳናወጣ ተከልክለናል ብለዋል።
“በአስመራ የሚገኘው ተወካያቸው ከሽያጭ የተሰበሰበ ገንዘብ ለማስገባት ሲል ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ እንደማይቻል ተነግሮታል፤ ይህ የሆነው ሐምሌ 20 በተጻፈ ደብዳቤ አማካኝነት ነው”
ከነሃሴ 25 በኋላ ሂሳባችሁ ታግዷል ለሀገር ውስጥ ወጪም መጠቀም አትችሉም መባሉን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ በረራውን ለማቋረጥ ተገደናል። "የበረራ ወጪያችንን መሸፈን ባለመቻላችን ተገደን ወጥተናል" ብለዋል ዋን ስራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርትራ ውስጥ የናቅፋ እና የሀርድ ከረንሲ (ዶላር) የሂሳብ ደብተር ያሉት ሲሆን፤ የናቅፋ አካውንት የቆየ እና የማይንቀሳቀስ የሂሳብ አካውንት መሆኑን ገልጸዋል።
የዶላር አካውንሩ ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኬት ሲሸጥ የነበረው በውጭ ምንዛሬ መሆኑን ገልጸው ይህንን ገንዘብም እገዳው እስከተላለፈበት ቀን ድረስ በተለያዩ ጊዜዎች ገንዘቡን ሲያንቀሳቅስ እንደነበረ ገልጸዋል።
በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ያወጣውን የጉዞ ክለከላ ተከትሎ የዶላር አካውን እንዳያንቀሳቅስ መከልከሉ በመግለጫቸው ተጠቁሟል።
አክለውም አየር መንገዱ ገንዘብ ካላገኘ እና እዛ ለሚያስፈልጉ ወጪዎች መጠቀም ካልቻለ በረራ ማቆም ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።
"አየር መንገዱከኤርትራ የወጣው ተገዶ ነው" ያሉት አቶ መስፍን ዋናው ችግሩ ለምን እንደታገድን አለማወቃችን ነው፤ በተጻፈው ደብዳቤም ላይ ምንም የተገለጸ ነገር የለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ከዛሬ ነሀሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ማቆሙን አስታውቋል።
ጉዞ ለማድረግ ቲኬት የገዙ መንገደኞችም በመረጡት አየር መንገዶች እንዲበሩ እንደሚያደርግ እና የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርግም አየር መንገዱ ገልጿል፡፡
የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በሚጓዙ ተጋዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ማንገላታት እንዲሁም ካሳ አለመክፈል የሚሉ ምክንያቶችን አስቀምጦ ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በወቅቱ ኤርትራ በአየር መንገዱ ላይ የጣለውን የበረራ ክልከላ መልሶ እንዲያጤነው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ ዳግም የጀመረው ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በ2011 ዓ.ም ላይ እንደበረ ይታወሳል።
በወቅቱ የመጀመሪያውን በረራ ወደ አስመራ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ዘመናዊ አውሮፕላን 250 ገደማ ሰዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ መጓዙም አይዘነጋም።