የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ መብረር አቆመ
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ሲያደርግ የነበረውን በረራ አቋርጫለሁ ብሏል
አስቀድመው የበረራ ጉዞ ቲኬት የቆረጡ መንገደኞች ያለምንም ዋጋ ጭማሪ በሌሎች አየር መንገዶች እንዲጓዙ እንደሚያደርግ አየር መንገዱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ መብረር አቆመ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ ከነገ ነሀሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንደሚያቆም አስታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ያለው አየር መንገዱ በኤርትራ ያለው አሰራር አስቸጋሪ እና ከቁጥጥሩ ውጪ መሆኑ ለበረራው መቋረጥ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
ጉዞ ለማድረግ ቲኬት የገዙ መንገደኞችም በመረጡት አየር መንገዶች እንዲበሩ እንደሚያደርግ እና የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርግም አየር መንገዱ ገልጿል፡፡
ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመስከረም 30 በኋላ ወደ አስመራ እንዳይበር መከልከሏ ይታወሳል፡፡
የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በሚጓዙ ተጋዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ማንገላታት እንዲሁም ካሳ አለመክፈል የሚሉ ምክንያቶችን አስቀምጦ ነበር
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በወቅቱ ኤርትራ በአየር መንገዱ ላይ የጣለውን የበረራ ክልከላ መልሶ እንዲያጤነው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
አክለውም “የኤርትራ ሲቪል አቬሽን አሁንም ውሳኔውን እንዲያጤነው እንጠይቃለን፤ ይህን የማይሆን ከሆነ የሚጎዱት ግን ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ናቸው” ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ ዳግም የጀመረው ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በ2011 ዓ.ም ላይ እንደበረ ይታወሳል።
በወቅቱ የመጀመሪያውን በረራ ወደ አስመራ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ዘመናዊ አውሮፕላን 250 ገደማ ሰዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ መጓዙም አይዘነጋም።