ገብረ ጉራቻ አቅራቢያ የሚፈጸመውን ተደጋጋሚ እገታ ለምን ማስቆም አልተቻለም?
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ባሉ ቦታዎች በየጊዜው እገታ ይፈጸማል
አሁን ድረስ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱት በጸጥታ ኃይሎች ታጅበው እንደሆነ አሽከርካሪዎች ገልጸዋል
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በዋና መንገድ ላይ በምትገኘው ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ንጹሃን መንገደኞች እና አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች ታገቱ የሚል ዜና በተደጋጋሚ ይሰማል።
ለ17 ዓመታት ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ሸቀጦችን በማመላለስ ስራ የተሰማሩ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አሽከርካሪ እንዳሉት ገብረ ጉራቻን ማለፍ ከባድ እንደሆነባቸው ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
"ሌላውን አስቸጋሪ እና ረጅም መንገድ ተጉዤ ገብረ ጉራቻን እስከማልፍ ድረስ ጭንቅ ይሆንብኛል፣ ቤተሰቦቼም ሁሉ ጉዞ ስጀምር እንደተጨነቁ ነው" የሚሉት እኝህ አሽከርካሪ "ሌላ ስራ እንዳልቀይር የማውቀው ሙያ ይሄ ነው ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኛል" ብለዋል፡፡
መንገዱን ሹፍርና ከመጀመሬም በፊት ሳውቀው ፍጹም ሰላም ነበር የሚሉት አሽከርካሪው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን በገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ያሉት አሊዶሮ እና ቱሉ ሚልኪ የሚባሉት ቦታዎች በተደጋጋሚ እገታዎች እየተፈጸሙ መሆኑን አክሏል፡፡
አሁን ላይ ከአማራ ክልል ደጀን እና ከአዲ አበባ በመንገዱ የሚተላለፉ ተጓዦች ያለ ጸጥታ ኃይል እጀባ እያለፉ እንዳልሆነ የተናገረው አስተያየት ሰጪው ካለ እጀባ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ መታገቱ የማይቀር መሆኑንም አክሏል፡፡
ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር ከ60 መንገደኞች ጋር በአውቶቡስ እየተጓዙ እያለ ለጥቂት ከእገታ መትረፋቸውን የሚናገሩት ሌላኛው መንገደኛ ደግሞ አውቶቡሱ ከቆመ በኋላ ሮጠው ካመለጡት መካከል አንዱ ነኝ ብለውናል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እኝህ አስተያየት ሰጪ ስድስት ታጣቂዎች በአውቶቡሱ ውስጥ ተሳፍረው እና ሮጠው ማምለጥ ያልቻሉ ከ30 በላይ ሴቶች እና ህጻናትን አግተው ሲወስዱ በአይናቸው ማየታቸውን ተናግረው እገታው የተፈጸመው ረፋድ 4፡45 አካባቢ እንደነበርም አክለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ከሄዱ በኋላ ሹፌሩን ጨምሮ ሮጠን አምልጠን የነበርን ቀሪ ተሳፋሪዎች እየተጓዝን እያለ እገታው በተፈፀመበት አንድ ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት ውስጥ ልዩ ስሙ ኩዩ ጂፕሰም ፋብሪካ አካባቢ ለነበሩ ሚኒሻዎች ብንነግራቸውም ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ሙከራ እና ፍላጎት እንዳልነበራቸውም ተናግረዋል፡፡
ታጣቂዎቹ መንገደኞችን ካገቱ በኋላ ከ500 ሺህ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ እየተቀበሉ ሲለቁ መቆየታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው ይህ ክስተት ሲደጋገም እና ወንጀሉን ለማስቆም ጥረቶች ሲደረጉ አለማየቱም አክሏል፡፡
ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ስትጓዝ ከሌሎች መንገደኞች ጋር የልጆቹ እናት ታግታ ከ21 ቀናት በኋላ መለቀቋን የነገረን ደግሞ ሌላኛው የእገታ ሰለባ ግለሰብ ነው፡፡
“የአውሮፕላን ቲኬት መግዣ ስላልነበረን ሚስቴ በአውቶቡስ እንድትመጣ ተስማማን፣ በመታገቷ ምክንያት ልጆቻችን ማሳደጊያ ይሆናሉ ያልናቸውን ጥሪቶች ሁሉ ሸጬ 500 ሺህ ብር ከከፈልኩ በኋላ ሚስቴ ከልጆቿ ጋር ተቀላቀለች፣ እንቁጣጣሽን በሀዘን እና ተስፋ በማጣት ነው ያሳለፍነው” ብሏል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ይህ አስተያየት ሰጪ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቸውን ሪፖርቶች፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተሰሩ ዘገባዎችን እና ሌሎች መረጃዎችን መሰረት አድርገን ባደረግነው ማጣራት ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካኝ በዓመት ከ2 እስከ 3 ጊዜ መንገደኞች በገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ታግተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙንኬሽን እና የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳድር በገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ እየተፈጸሙ ያሉ እገታዎችን በተመለከተ ምላሻቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡