ከአንድ ሳምንት በፊት ገብረ ጉራቻ ላይ በታጣቂዎች የታገቱ ሰዎች ጉዳይ ከምን ደረሰ?
ከዚህ በፊት በዚሁ ስፍራ ከደባርቅ ዩንቨርሲቲ በመመለስ ላይ እያሉ የታገቱ ሰዎች ግማሽ ሚሊዮን ብር ከፍለው መለቀቃቸውን ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ልዩ ባስ ትራንስፖርት ማህበራትና ድርጅቶች ህብረት በበኩሉ በሾፌሮች እና ተሳፋሪዎች ላይ በሚፈጸሙ እገታዎች ምክንያት ስራ መስራት እንዳልቻሉ ተናግሯል
ከአንድ ሳምንት በፊት ገብረ ጉራቻ ላይ በታጣቂዎች የታገቱ ሰዎች ጉዳይ ከምን ደረሰ?
ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ከደባርቅ ዩንቨርሲቲ ተነስተው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ ተማሪዎች እና ሌሎች መንገደኞች መታገታቸው ይታወሳል፡፡
እገታው የተፈጸመው ለአዲስ አበባ ከተማ ትንሽ ሲቀራቸው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾም ነበር፡፡
በዚሁ ተመሳሳይ ስፍራ እና ሰዓት ከአንድ ሳምንት በፊት ነሀሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበሩ መንገደኞች በታጣቂዎች ታግተዋል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የታጋች ቤተሰብ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ከዘጠኝ ቀን በፊት የቤተሰባችን አባል ወደ ደብረ ማርቆስ በመጓዝ ላይ እያሉ ከነ ልጆቿ በታጣቂዎች ታግታለች፣ የት እንዳለች አናውቅም ብለውናል፡፡
በወቅቱ ከእገታው ያመለጠ አንድ ሰው ስለ እገታው መስማታቸውን የሚናገሩት እኝህ አስተያየት ሰጪ አብዛኞቹ ታጋቾች ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን ጉዳዩን ለጸጽታ ተቋማት ማሳወቃቸውንም አክሏል፡፡
ይሁንና እስካሁን የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ሙከራ ስለማድረጋቸው ወይም ምን አይነት ጥረቶችን እያደረጉ እንደሆነ አናውቅም ያሉት አስተያየት ሰጪው በጎን ግን ታጣቂዎቹ 500 ሺህ ብር እንድንልክ እያስጨነቁን ነውም ብሎናል፡፡
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አስተያየት ሰጪ እና ከእገታው ሮጦ ያመለጠ እማኝ በበኩሉ እገታው ገብረጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ነሀሴ 23 ቀን ረፋድ 4፡45 ላይ ነው መፈጸሙን ነግሮናል፡፡
በወቅቱ ታጣቂዎቹ ጥይት እየተኮሱ ነበር እኛ የተሳፈርንበት አውቶቡስ ታጣቂዎቹ ጋር ሳይደርስ አቁሞ ስለ ነበር እሱን ጨምሮ ብዙ ተሳፋሪዎች ወርደን በእግራችን ሮጠን ማምለጥ ቻልን ሲልም ተናግሯል፡፡
አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ተማሪዎችን እና ንጹሃን ዜጎችን ማገት እንዲቆም ጠየቀች
ከሁለት ወር በፊት ከደባርቅ ዩንቨርሲቲ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ ተማሪዎች እና ሌሎች መንገደኞች መታገታቸው ይታወሳል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በወቅቱ ስለ ጉዳዩ ጉዳዩን የዘገበ ሲሆን አሁን ምን ላይ እንዳሉም ጠይቋል፡፡
የታጋች ቤተሰቦች በወቅቱ ቤተሰቦቻቸው ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመከፋፈል እንደወሰዷቸው እና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ካልከፈሉ እንደሚገድሏቸው ተናግረው ነበር፡፡
እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉን አሁን ላይ ቤተሰቦቻቸው ከ40 ቀናት እገታ በኋላ ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር ከከፈሉ በኋላ እንደተለቀቁላቸው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ምን አይነት ድጋ አደረገላችሁ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም ቤተሰቦቻችንን ከታጣቂዎች እገታ እንዲያስለቅቅልን ጥያቄ በተደጋጋሚ ብናቀርብም በሐሰት ታግተው የነበሩት ተለቀዋል የሚል ዘገባ ከማሰራት ውጪ ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገልንም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልዩ ባስ ትራንስፖርት ማህበራትና ድርጅቶች ህብረት በበኩሉ በየቦታው በሚደረጉ የእገታ ወንጀሎች ምክንያት ስራ መስራት እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡
የማህበሩ አቶ ሙሉቀን መለሰ ለአል ዐይን እንዳሉት በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በየጊዜው በሚፈጸሙ እገታዎች ሹፌሮችን ጨምሮ በተሳፋሪዎች ላይ ግድያ፣ ንብረት ውድመት እና ዘረፋ እየተፈጸመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰፊ ስራ የነበረባቸው ክልሎች ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ላይ እገታው መስፋፋቱን የሚናገሩት አቶ ሙሉቀን በዚህ ምክንያት የአውቶቡስ ባለ ንብረቶች ከስራው እየሸሹ እና እየወጡ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ጉዳዩን ለመንግስት ስናቀርብ ሀገራዊ ጉዳይ ነው ከማለት ውጪ ምንም ምላሽ እየሰጡን አይደለም የሚሉት ሊቀመንበሩ ችግሩ የሚፈታው በፖለቲካ መፍትሔ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙንኬሽን ቢሮ እና እገታው በተደጋጋሚ የሚፈጸምበት ወረዳ ሰሜን ሸዋ ዞን ሃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባሳለፍነው ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተራዘሙ ግጭቶች ምክንያት የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው ቀጥለዋል ማለቱ ይታወሳል።
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች መባባሳቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ አደረኩት ባለው ማጣራት ለዘረፋ "በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች" እገታዎች እንደሚፈጸሙ አረጋግጫለሁም ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በበኩሉ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተራዘሙ ግጭቶች የህግ የበላይነት እንዳይከበር ምክንያት ሆነዋል ማለቱ አይዘነጋም፡፡
በተከታታይ የተፈጸሙ ያሉ እገታዎች ወንጀለኞችን እንዳይጠየቁ ማድረጉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አረቪን ማሲንጋ መናገራቸውን ኢምባሲው አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ማሲንጋ አክለውም ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ተማሪዎችን እና ንጹሀንን ማገት መቆም አለበት ሲሉ ያሳሰቡ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግስት በበኩሉ ታግተው የነበሩ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የጸጥታ ሀይሎች ባደረጉት ህግ ማስከበር ከታጣቂዎች ማስለቀቃቸውን ቢያሳውቅም የታጋች ቤተሰቦች ግን ልጆቻቸው እንዳልተለቀቁ በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡