ስምምነቱ በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ያለው የይገባኛል ጥያቄ ስጋት በጨመረበት ወቅት ነው የመጣ ነው
ፊሊፒንስ በዚህ ሳምንት ለአሜሪካ የጦር ሰፈሮቿን እንድትጠቀም ሰፊ በር ከፍታለች።
ቻይና በታይዋን ያላት የግዛትና በአወዛጋቢው የደቡብ ቻይና ባህር ላይ ባላት ሰፊ የይገባኛል ጥያቄ ላይ ስጋት በጨመረበት ወቅት ነው ፊሊፒንስ የጦር ሰፈሮቿን የፈቀደችው።
አሜሪካ እና ፊሊፒንስ ምን ተስማሙ?
ፊሊፒንስ ለአሜሪካ ተጨማሪ አራት የጦር ሰፈሮችን ፈቅዳለች። ሀገሪቱ በፈረንጆቹ 2014 በተሻሻለው የመከላከያ ትብብር ስምምነት መሰረት ነው ፈቃዱን የሰጠችው።
ይህም አሜሪካ የምትጠቀማቸውን አጠቃላይ ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ አድርሷል።
የጦር ሰፈሮቹ የት እንደሚገኙ ግን አልገለጸም።
የማኒላ የቀድሞ ወታደራዊ አዛዥ ባለፈው ዓመት ዋሽንግተን ለታይዋን ቅርብ በሆነው ሉዞን ደሴት የሚገኘውን የጦር ሰፈር ጠይቃለች ብለዋል።
ጣቢያዎቹ "ስልታዊ አካባቢዎች" እንደሚሆኑ እና ምናልባትም የባህር ኃይል መገልገያዎችን ሊያካትቱ እንደሚችሉ ባለሞያዎች ጠቁመዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ፊሊፒንስ ለአሜሪካ በጣም አስፈላጊ የሆነችው ለምን ነው?
ፊሊፒንስ የቀድሞ የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ስትሆን እ.አ.አ በ1951 ነጻነቷን ካገኘች ከአምስት ዓመታት በኋላ የአሜሪካ አጋር ሆናለች።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በኮሪያ እና በቬትናም ውስጥ ለነበሩት ጦርነቶች አስፈላጊ የሆኑ የአሜሪካን ትላልቅ የባህር ኃይል ማዕከሎችን አስተናግዳለች።
ፊሊፒንስ ለታይዋን በጣም ቅርብ ስትሆን፤ ከሉዞን ሰሜናዊ ጫፍ 200 ኪሜ እርቀት ላይ ትገኛለች።
ባለሞያዎች እንደሚናገሩት ሉዞን ታይዋን በቻይና ብትወረር ለመመከት የሚያገለግሉ ሮኬቶች፣ ሚሳይሎችና የጦር መሳሪያዎች መገኛ ቦታ እንድትሆን አሜሪካ ከፍተኛ ፍላጎት አላት።