ቻይናን ያስቆጣው የአሜሪካዋ ምክትል ፕሬዝዳንት የፊሊፒንስ ጉብኝት
ምክትል ፕሬዝዳንቷ የጎበኙት የፓላዋን ደሴት ቻይና የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበት ስፍራ ነው ተብሏል
ቤጂንግ፤ የዋሽንግተን አካሄድ በቀጠናው ያለኝን የበላይነት ሊያሳጣኝ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮባታል
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ማክሰኞ እለት በፊሊፒንስ የሚገኘውን የፓላዋን ደሴት ጎብኝተዋል።
የካማላ ሃሪስ ጉብኝት አሜሪካ ለፊሊፒንስ ያላትን የቆየ አጋርነት ለማሳየሳት ያለመ እንደሆነ ቢነገርም፤ በቻይና በኩል ቁጣን እንደቀሰቀሰ እየተነገረ ነው።
ምክንያቱ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንቷ የጎበኙት የፓላዋን ደሴት ቻይና የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበት በመሆኑ ነው ተብሏል።
የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቻይና የምታነሳው ጥያቄ ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው ቢልም፤ ቤጂንግ ሉዓላዊነቴ ያንን ባህር ከሞላ ጎደል የሚያካትት ነው ብላ እንደምትሞግት ይታወቃል።
እናም ቤጂንግ፤ የዋሽንግተን አካሄድ በአከባቢው ያለኝን የበላይነት ሊያሳጣኝ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባት የሮይተረስ ዘገባ ያመለክታል።
የተወሰኑ የደቡብ ቻይና ባህር ክፍሎች በፊሊፒንስ እንዲሁም በቬትናም፣ ማሌዥያ እና ብሩኒ ይገባኛል ጥያቄ እንደቀረበባቸው ይታወቃል።
ከጉብኝቱ አስቀድሞ አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ካማላ ሃሪስ በፊሊፒንስ ጉብኝታቸው በሚያደርጉት ንግግር ላይ “የዓለም አቀፍ ህግ አስፈላጊነት፣ የሕጋዊ ንግድ ነጻነት እና የመርከብ ነጻነት” አጽንዖት ይሰጣሉ ብለው ነበር።
እንደተባለውም ሃሪስ ማኒላ ውስጥ ከፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች በተወያዩበት ወቅት ሀገራቸው ለፊሊፒንስ ያላትን “የማያወላውል” ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የጆ-ባይደን ምክትሏ ሃሪስ “የደቡብ ቻይናን ባህርን በሚመለከት ዓለም አቀፍ ህጎችን እና ደንቦችን በመደገፍ ከፊሊፒንስ ጎን እንቆማለን”ም ብለዋል፡፡
በደቡብ ቻይና ባህር በሚገኘው የፊሊፒንስ ጦርን፣ የመንግስት መርከቦችን ወይም አውሮፕላኖችን ላይ ጥቃት ቢሰነዘር አሜሪካ ወታደራዊ አጋርነቷን ለማሳየት ዝግጁ መሆኗም ተናግረዋል፡፡
ለቤጂንግ ቅርብ በነበሩት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱተርቴ የስልጣን ዘመን ሻክሮ የቆየው የፊሊፒንስ እና አሜሪካ ግንኙነት አሁን ላይ መልካም የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱ ይነገራል።