ራኒል ዊክረሜሲንጌ የስሪላንካ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆኑ
ዊክረሜሲንጌ ህግ እና ስርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ "በአማጺያን" ላይ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብለዋል
ስሪላንካ በሳምንት ውስጥ አዲስ ፕሬዝዳንት እንደምትመርጥ የሀገሪቱ አፈ-ጉባኤ ማሂንዳ ያፓ አስታውቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሬሜሲንግ ጊዜያዊ የስሪላንካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሸሙ፡፡
ዊክረሜሲንጌ ፓርላማው በሀገሪቱ የተከተለውን ተቃውሞ ተክተሎ ወደ ሲነጋፖር የኮበለሉትን ጎታባያ ራጃፓክሳን ተተኪ እስኪመርጥ ድረስ የስሪላንካ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በተቃውሞ አመጽ ከሀገራቸው የተሰደዱት የስሪላንካው ፕሬዝዳንት ጎታብያ ራጃፓክሳ ከስልጣን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በትናንትናው እለት መላካቸው የሚታወስ ነው።
የፕሬዝዳንቱ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት ማግኘቱም የሲሪላንካ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ማሂንዳ ያፓ በዛሬው እለት አስታውቀዋል፡፡
"ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሕገ መንግስቱ መሰረት አዲስ ፕሬዚዳንት ወደ መሾም እንሸጋገራለን" ነበር ያሉት አፈ-ጉባኤው ከሰአታት በፊት በሰጡት መግለጫ።
በዚህም መሰረት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ራኒል ዊክረሜሲንጌ ጊዜያዊ የሲሪላንካ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ተገልጿል፡፡
ራኒል ዊክሬሜሲንግ ጊዜያዊ የስሪላንካ ፕሬዝዳንት ሆነው ለማገልገል ቃለ መሃላም ፈጽመዋል፡፡
ዊክሬሜሲንግ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፕሬዚዳንትነት ስልጣንን ለመከለስ እና ፓርላማን ለማጠናከር የሚያስችሉ የህገ-መንግስት ማሻሻያዎች አደርጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል ።
ህግ እና ስርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ "በአማጺያን" ላይ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁም ብለዋል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ።
ብዙ ወታደሮች የቆሶሉበትን የእሮብ ምሽት በፓርላማ አከባቢ የተፈጠረውን ብጥብጥ በተመለከተ ሲናገሩም “እውነተኛ ተቃዋሚዎች በእንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ውስጥ አይገቡም” ሲሉ ተችተዋል ዊክረሜሲንግ ፡፡
"በተቃዋሚዎች እና በአማቲዎች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤በአማጽያን ላይ ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉም ዝተዋል።
ራኒል ዊክረሜሲንጌ ይህን ይበሉ እንጅ፤ በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት የሚያገለግሉት ምናልባትም ከሳምንት ላልበለጡ ጊዜያት ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡፡
የስሪላንካ አፈ-ጉባኤ ማሂንዳ ያፓ የሀገሪቱ የሕግ አውጭ አካላት አዲስ መሪን ለመምረጥ በነገው እለት ለስብሰባ ይቀመጣሉ እንዲሁም በሰባት ጊዜ ውስጥ አዲስ ፕሬዝዳንት ይመረጣሉ ብለዋል፡፡
በህግ አውጪ አካላት የሚመረጡት አዲስ ፕሬዝዳንት የራጃፓክሳን ቀሪ የስልጣን ዘመናት ማለትም አስከ 2024 ድረስ እንደሚያገለግሉም ነው የተናገሩት፡፡
በሳምንት ውስጥ የሚመረጡት አዲስ ፕሬዝዳንት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሾም ስልጣን እንዳላቸውም አስታውሰዋል አፈ-ጉባኤው፡፡
አሁን በጊዜያዊነት የተመረጡት ራኒል ዊክረሜሲንጌ የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው አጽንተው ለመቀጠል የሚያስችል የፓርላማ ድጋፍ ያገኛሉ ወይስ ሌላ አዲስ መሪ ብቅ ይላል ለሚለው ግን አፈ-ጉባኤው ምንም የሰጡት ፍንጭ የለም፡፡