ዊል ስሚዝ “ለአካዳሚው አልታመንኩም” በሚል ከኦስካር አካዳሚ ለቀቀ
የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዴቪድ ሩቢን የስሚዝ መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል
የፈጸምኩትን ድርጊት ተከትለው የሚመጡ " ተጨማሪ ቅጣቶች" ካሉ ለመቀበል ዝግጁ ነኝም ብሏል ስሚዝ
ዊል ስሚዝ በኦስካር የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ የሙያ አጋሩ የሆነውን ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን በጥፊ በመምታቱ "የአካዳሚውን እምነት ክጄያለሁ" በሚል ከሆሊውድ የሞሽን ፎቶግራፍ ጥበብ እና ሳይንስ አካዳሚ (ኦስካር) ለቀቀ፡፡
የፈጸምኩትን ድርጊት ተከትለው የሚመጡ " ተጨማሪ ቅጣቶች" ካሉ ለመቀበል ዝግጁ ነኝም ብሏል ዊል ስሚዝ፡፡
ዊል ስሚዝ በ94ኛው የአካዳሚው ሽልማት ላይ የፈጸምኳቸው ድርጊቶች “አስደንጋጭ እና ይቀር የማይባሉ ናቸው”ሲልም ጸጸቱን ገልጿል ።
“ለአካዳሚው አልታመንኩም፤ ሌሎች ተሿሚዎችና ተሸላሚዎች ባደረጉት ድንቅ ስራ የማክበር እና የመከበር እድል ነፍጌአለሁ” የሚለው ዊል ስሚዝ፤ በዚህ ምክንያት ከአካዳሚው ለመልቀቅ ደብዳቤ ለማስገባት መገደዱንም አስታውቋል፡፡
የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዴቪድ ሩቢን የስሚዝ መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል።
"በሚስተር ስሚዝ ላይ የአካዳሚው የስነ-ምግባር መርሆዎች በመጣሳቸው በአካዳሚው ህግ መሰረት ሊከተሉ የሚችሉ ቅጣቶች ካሉ ፤ ሚያዝያ 18 ከምናደርገው የቦርድ ስብሰባ በተጨማሪ ነገሮችን የምንመለከት ይሆናል"ም ብለዋል የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ።
ዊል ስሚዝ፤ ከአካዳሚው መልቀቁ ከአሁን በኋላ ለእጩዎች ድምጽ የመስጠትና የመምረጥ መብት እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ብዙም የማይታዩ ጥቅማጥቅሞችን የሚያገኝ ይሆናል፡፡
እውቁ የሆሊውድ ተዋናይ የሙያ አጋሩ ክሪስ ሮክን በጥፊ የመታበት ክስተት እስካሁን በርካቶችን እንዳስገረመ ነው። በወቅቱ በስሜት ለፈጸምኩት ድርጊት ይቅርታ አድርጉልኝ ማለቱ አይዘነጋም።
ከድርጊቱ በኋላ የኦስካር ሽልማቱን ሲቀበል “ፍቅር የእብድ ስራ እንድትሰሩ ያደርጋል" የሚል በስሜት የተዘበራረቀ ንግግር ማድረጉም እንዲሁ ይታወሳል፡፡