ዝነኛው ኢትዮጵያዊ ተወዛዋዥ በታዋቂው ‘ቴድ ቶክ’ ላይ ንግግር ሊያደርግ ነው
7 ሰው ተመድቦለት 3 ወር ሙሉ በምትሰጠው ደቂቃ ንግግር ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግሯል
ተወዛዋዡ ‘ፌሎው’ ሆኖ ለመድረኩ የተመረጠ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው ተብሏል
የታዋቂው ‘ቴድ ቶክ’ የዘንድሮ ‘ፌሎው’ ሆነው ከተመረጡ 20 ሰዎች መካከል አንዱ ዝነኛው ኢትዮጵያዊ ተወዛዋዥ እና የዳንስ ኬሪዮግራፈር መላኩ በላይ ነው፡፡ መላኩ 5 አህጉራትንና 14 ሃገራትን ካካለለው ምርጫ አንዱ ሆኖ የተመረጠው በድንቅ ተወዛዋዥነቱና በኢትዮጵያ ባህል አምባሳደርነቱ ነው፡፡ ‘ፌሎው’ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ መመረጡንም ፕሮግራሙን የተመለከቱ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የፈንድቃ ባህል ማዕከል መስራች እና ባለቤቱ መላኩ በቀጣዩ ወር ሚያዚያ የመጀመሪያ ሳምንት (APRIL 10 – 14 ) በካናዳ ቫንኩቨር በሚዘጋጅ ዓለም አቀፍ መርሐ ግብር ላይ ንግግር የሚያደርግም ይሆናል፡፡ የባህል አምባሳደሩ መላኩ እንዴትና ምን ሰርቶ እንደተመረጠ፣ በመመረጡ ስለተሰማው ነገር እና የሚያደርገውን ንግግር በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡ እንዲያነቡት ጋበዝን፡፡
አል ዐይን ፡ በቅድሚያ የመመረጡን እድል በማግኘትህ እንኳን ደስ ያለህ
መላኩ ፡ አመሰግናለሁ
አል ዐይን ፡ ‘ቴድ ፌሎው’ ምንድነው ?
መላኩ ፡ እኔም አሁን ከተመረጥሁ በኋላ ነው የበለጠ ያወቅሁት፡፡ ከዚህ በፊት አየዋለሁ፤ ‘ቴድ ፌሎው’ ይሁን ሌላ እኔንጃ፡፡ ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በዓለም ላይ የሚቀርቡበት መድረክ ነው፡፡ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ አርዓያ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ‘አክቲቪስቶች’ ወይም አርቲስቶች ናቸው የሚቀርቡበት፡፡ እና የእኔንም ስመለከት ወደ 1 ሺ 700 ገደማ ተወዳዳሪዎች ነበሩ ከዚያ ውስጥ ነው 20ዎቻችን የተመረጥነው፡፡ እዛ ሄደን ንግግር እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ እዛ ውስጥ ለመግባት ምን መስራት እንዳለብህ ማሰብ አያቅትም፡፡
አል ዐይን ፡ ምን ሰርተህስ ነው የተመረጥከው?
መላኩ ፡ ይመስለኛል ፈንድቃ ውስጥ በምናደርገው እንቅስቃሴና በምንሰራው ስራ ነው፡፡ በመላው ዓለም ስሄድ በዳንሱ፣ በጭፈራው ነው በብዛት ድልድይ የሆነኝም እሱ ነውና ከህዝቤም ጋር የሚያገናኘኝ ትከሻዬ ነው ይሄ ጭፈራው፡፡ ከዛ አልፎ ደግሞ ድልድይ ሆኖ ከሃገር ውጭ ካለው ከዓለም ህብረተሰብ ጋር ያገናኘን ጭፈራው ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሰራኋቸው ስራዎች ተጽዕኖ ፈጥረው ነው እንግዲህ እዚህ ያደረሱኝ፡፡ በቃ የሚታወቅ ነው፤ ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ብዙ ነገር ነው የሰራሁትኝ፡፡
አል ዐይን ፡ ፈንድቃ ውስጥ ምንድነው የሰራኸው?
መላኩ ፡ ለመጥቀስ ከተፈለገ በአዝማሪው ነው ስሰራ የነበረው፡፡ 12 ዓመት ያለ ደሞዝ፤ እኔ ብቻ አይደለሁም ሁሉም አዝማሪ አዲስ አበባ ውስጥ ደሞዝ የለውም፤ በሽልማት ሰርቻለሁ፡፡ ፈንድቃን ከመሰረትኩ በኋላ ደሞዝ በመጀመር ያላቸውን የሙዚቃ ተሰጥዖ ‘ኬሮግራፍ’ ‘ኮምፖዝ’ በማድረግ ወደ ህዝቡ በደንብ እንዲያቀርቡና በስራቸው የመተዳደር አቅም እንዲኖራቸው ከሃገር አልፎ ወደ ዓለም እየወሰድኩኝ እንዲገናኙ አድርጌ ራሳቸውንም ሃገራቸውንም የጠቀሙ ብዙ አርቲስቶች አሉ፡፡
ካዛንቺስ አካባቢ ብዙ አዝማሪ ቤቶች ነበሩ ሆኖም መልሶ ማልማት በሚል ሰበብ እንዳለ ፈርሰዋል፡፡ ይሄን ቤት (ፈንድቃን) ገዝቼ በማስቀረት አሁን አዝማሪ ብቻ አይደለም የህጻናት ፕሮግራም አለ፣ ነጻ ቤተ መጻህፍት፣ የስዕል፣ የሙዚቃ፣ የሸክላ፣ የጥጥ መፍተል ፕሮግራም ለህጻናቶች አለ፡፡ ‘ጋለሪ’ውን በነጻ በመስጠት ቋሚ የስዕል ኤግዚቢሽን አለ፡፡ አዳዲስ አርቲስቶች በየሶስት ሳምንቱ ስራቸውን በነጻ ያቀርባሉ፡፡ እንደዚሁም ጃዝ ሙዚቃ በሚገርም ሁኔታ ሃገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ፤ ሙዚቀኞች ጃዝ ያቀርባሉ፡፡ ኢትዮ ከለር ሶስት ትውልድ ይዞ ጃዝ ያቀርባል፡፡ የግጥም ፕሮግራም፣ ‘ቪዥዋል አርት’ አለ፡፡ 24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል፤ ፈንድቃ፡፡ እና በዚህም የተነሳ ነው እንግዲህ የዓለም ሎሬትም ብደረግ፤ ኔዘርላንድ ‘ፕሪስክላውስ አዋርድ’ ያገኘኹት በነዚህ ስራዎች ተጽዕኖ ነው፡፡
አል ዐይን ፡ ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ የሚሰሩትን ጨምሮ በመስራትህ ምን አገኘህ?
መላኩ ፡ የሃገር ውስጥ የበጎ ሰው የአርዓያ ሰው ተሸላሚ ነኝ፡፡ ከአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሚል ከሞሮኮ እንደዚሁም ከኳታር ዋንጫ፤ የፈረንሳይ የክብር ሜዳሊያ ‘ሸቫ ዲ ሎነር’ የሚሉት አግኝቻለሁ፡፡ ከዓለም 200 ሰው ሲመረጥ ከአፍሪካ ሶስት ነበርን፡፡ ስለዚህ ይሄ ሁሉ ስራ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ይሄ ሚዛን ደፍቶ ነው በውዝዋዜው በጭፈራውም ጥበብ ብዙ ነገር እየሰራሁ ያለሁትኝ፡፡ ውዝዋዜ ወይም ጭፈራ እንደ ጥበብ አይታይም ኢትዮጵያ ውስጥ፤ በጣም የተናቀ ነው፡፡ ለእሱም ደግሞ ትግል በማድረግ ከሞያ ጓደኞቼ ጋር የኢትዮጵያ ተወዛዋዦች ጥበብ ማህበር ከመሰረቱት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ቢሮውም ራሱ ቦታ ሰጥቼ እዚሁ ፈንድቃ ነው፡፡ ከዩኔስኮ ድጋፍ አግኝተን ሌሎች ቅርንጫፎችን በክልሎች ሐዋሳ ላይ አቋቁመናል፤ ድሬዳዋ እና ሐረር ደግሞ እያቋቋምን ነው፡፡ እንደዚሁም ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሃገራዊ ጥበባዊ ስራዎችን ሲያወዳድር ማህበሩን ወክለን በውድድሩ ተሳትፈን ተረስቶ የነበረውን የውዝዋዜ ጥበብ አንጋፋዎቹንም ወጣቶቹንም እንዲሸለሙ ይሄ ማህበር ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ይሔ ሁሉ የመጣው እዚህ ፈንድቃ ውስጥ በምንሰራው ስራ ነው፡፡
እና ህብረተሰቤ የሰጠኝን መልሶ በመስጠት ያሳደገኝንን ለመጪው ትውልድ የምችለውን ለማበርከት በመታገሌ ነው እነዚህ ውጤቶች ደግሞ አልፈው ተርፈው ምሳሌ ሆነው አሁን ካናዳ ቫንኩቨር ሄጄ ንግግር እንዳደርግ እድሉን የፈጠረልኝ እነዚህ የስራ ውጤቶቼ ናቸው፡፡
አል ዐይን ፡ ‘ቴድ ቶክ’ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ነው፡፡ በዚያ መድረክ ላይ ንግግር እንድታደርግ በመመረጥህ ምን ተሰማህ?
መላኩ ፡ ትልቅ መድረክ ነው ያስፈራል፤ እንግዲህ ገና ሚያዚያ ላይ ነው እዛው ሄጄ ንግግር የማቀርበው፡፡ ንግግሩን ወደ ሰባት ሰው ተመድቦልኝ በ‘ዙም’ (በበይነ መረብ የቪዲዮ ግንኙነት) ሃሳቤን እያገዙኝ ነው፡፡ ሃሳቡን እሰጣቸዋለሁ ግን በምን መልኩ እንደማወራ ያግዙኛል ማለት ነው፡፡ በየሳምንቱ በዙም እየተገናኘን ሰው ተመድቦልኝ ‘እንትን’ እያልኩ ነው፡፡
አል ዐይን ፡ የምታወራበትን ርዕሰ ጉዳይ መርጠሃል?
መላኩ ፡ መርጫለሁ፡፡ ለሰላም ነው ‘ዴዲኬትድ’ ያደረግሁት ፡፡ መታወሻነቱ ለሰላም ይሁንልኝ የሚል ነው፡፡
አል ዐይን ፡ መላኩ መድረኩ ላይ ለመቅረብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ነው የሚል መረጃን ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ በመሆኑ የሚሰማህ ነገር አለ?
መላኩ ፡ እኔ ያው የመጀመሪያ የመጨረሻ በሚለው ሳይሆን እዚህ ውድድር ላይ መግባት ከባድ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሃገርን ይዘህ ስትገባ ደስ ይላል፡፡ እኔ ብዙ ትኩረት የማደርገው ብቻ ሚዛን ደፍተህ ሃገርህን ይዘህ እዛ ጋ ማስገባት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ እሱ ነው ለእኔ ደስ ያለኝ፡፡ እንደገና ደግሞ ምላሹ አበረታች ነው፤ ደስ ይላል ማለት ልፋትህን የሚረዳልህ ከአህጉር አልፎ ወደ ዓለም የሚደርስበት መንገድ ምክንያት ስትሆን ያኮራልና ደስ ይላል፤ በጣም ደስ ይላል፡፡
አል ዐይን ፡ ከአሁን ቀደም ‘ቴድ ቶክ’ን በመሰሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተገኝተህ ንግግር አድርገህ ታውቃለህ?
መላኩ ፡ አላውቅም! እኔ ያው እንዳልኩህ ሽልማቶች ላይ ንግግር አደርጋለሁ፡፡ ሃርቫርድን ጨምሮ በተለያዩ ብዙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ‘ወርክ ሾፕ’ እሰጣለሁ፤ ሰጥቻለሁም፡፡ በአንደኛ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም፡፡ ግን እንደዚህ ዐይነት በጣም ከባድ ነው፤ አራት ደቂቃ ነው የተሰጠኝ፡፡ ለአራት ደቂቃ ሶስት ወር ሙሉ ሰባት ሰው ተመድቦልኝ ‘እንትን’ እናደርጋለን፡፡ አንድ 500 ገጽ ማንበብ ይሻላል ከባድ ነው አራት ደቂቃ ለማቅረብ ከመታገል፡፡ እና ከባድ ነው እሱን እንግዲህ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው እሱ ከፊት ይቅደም፡፡ ሁሌም እሱ እየቀደመልኝ ነው ነገሮችን እየባረከልኝ እና እሱ የተመሰገነ ይሁን፡፡
አል ዐይን ፡ በመድረኩ ንግግር በማድረግህ ምንድን ነው የምታገኘው?
መላኩ ፡ አንዳንዴ ሲቸግር ለጓደኛ ራሱ ስትናገር እኮ ይቀልልሃል፡፡ ይሄ ትልቅ መድረክ ነው፤ ትልቅ መድረክ ላይ ደግሞ የሰው ልጆች በሰላም እንዲኖሩ ስለ ሰላም ነው ማውራት የምፈልገው፡፡ ስለ ሰላም ለአንድ ሚዲያ ተናግረህ የተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚሰማ ሲሆንና ዓለም ላይ የሚሰማ ሲሆን ይለያያል፡፡ ተደራሽነትን፤ ኢትዮጵያ ስለ ሰው ልጆች እንደምታስብ ድንበር የሌለው ጸሎት እንደምታደርግ ያን ማካፈልህ እንዴት አያኮራ፤ ደስ አይልህ፡፡ ሃሳብህን ትተነፍሳለህ፡፡ ሀገሬ እኔ ልብ ውስጥ ነች፤ እኔ ሃገሬ ውስጥ ነኝ፡፡ እና ይሄን በልቤ ይዤ ኢትዮጵያ ሁሌም በርሃብ በጦርነት ብቻ ሳይሆን ስለ ሰላም፤ ስለ ሰው ልጆች እንደምታስብ እንደምትጸልይ ለማሳየት ነው፡፡
አል ዐይን ፡ በተሳትፎው ሊሰጥ የሚችል የተለየ ሽልማት ወይ እውቅና አለ?
መላኩ ፡ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ እኔ እንደነገርኩህ ይሄ ሽልማት አለ ብዬ አልሰራም፡፡ የልቤን የምችለውን ‘ኮንትሪቢዩት’ ለማድረግ ነው፡፡ ሆኖም ይሄን ተመልክተው ያገዙኝ አሉ፡፡ እና እዚህ ላይ ቀርቦ በርሃብና በጦርነት ብቻ ስለሚያውቋት ስለ ኢትዮጵያ ገጽታ ለማስተካከል ነው፡፡ ለውስጥም ‘ሎካሉ’፤ እንደገና ሙያው ጭፈራው ነው እዛ ጋ የደረሰው፤ ጭፈራው ነው ሎሬት የሆነው፤ ይሄ ጭፈራ ነው ሚዛን የደፋውና ያሸነፈው እና እዚህ ግን ጭፈራ ሴት ልጅ ስታረግዝ ትባረራለች፣ ወንድ ልጅ ጨፍሮ እድሜው ሲገፋ ይባረራል፤ ያለ ጡረታ፡፡ በዚያ ላይ አጃቢ እንጂ ባለሙያ አይመስለውም ራሱ አርቲስቱ፡፡ ስለዚህ ይሄ ግንዛቤ በጣም የተራራቀ ስለሆነ ሙያተኛው ህብረተሰቡ ራሱ የጭፈራ ‘ቫሊዩ’ ምን እንደሆነ ማሳያ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
አል ዐይን ፡ ሰላምን እንዴት በርዕሰ ጉዳይነት መረጥከው?
መላኩ ፡ ሰላምን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ፍትህን የመሰለ ነገር የለም፡፡ የመረጥኩት ከድሮ ጀምሮ ነው፡፡ፍትህ፣ ነጻነት፣ እውነተኛ ዲሞክራሲ፤ በነጻነትና ተኮርኩሞ ያደገ ልጅ አንድ አይደለም፡፡ ነጻነት ሲባል አፍሪካ ውስጥ ብቻ አይደለም፤ ፍትህ ሲባል ዓለም ላይ ተጓድሏል፡፡ የፍትህ መጓደል ነው የራሽያ እና የዩክሬን ጦርነት፡፡ እና እነዚህ ነገሮች በጥበብ ነው የሚድኑት፡፡ ሰው ከጥበብ ጋር እንዲታረቅ ምልከታ መስጠት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገር ሰው ከጥበብ እንዲታረቅና ወታደሩ መሳሪያውን ጥሎ ወይ ሳክስፎን ወይ ማሲንቆ ቢጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ያን ዐይነት ስሜት ለማጋባት ትልቅ እድል ነው፡፡
አል ዐይን ፡ መላኩ ከ4 ደቂቃዋ ንግግር ውጭ የሚያቀርበው ሌላ ነገር አለ?
መላኩ ፡ ጠይቀውኝ ነበር ብቻዬን እንዳቀርብ፡፡ ሆኖም አይ ይሄ ትልቅ ውድድር ነው ከነ ሙሉ ክብሩ ነው ይዤ መምጣት ያለብኝ ብያቸው የባንዱን አባላት ብዛት ስነግራቸው ወጪውን አልቻሉትም፤ ምክንያቱም ለ20 ሰው ሁሉን ነገር ችለው ነው የሚወስዱን፡፡ ስለዚህ እዛ ምን ዐይነት ባንድ ጋር ብለውኝ ጃዝ ቢሆን ደስ ይለኛል አልኳቸው፤ በቃ ሲዲውን ምኑን እንልክልሃለን አሉኝ፤ ‘ኖ’ እንዳውቃቸውም አልፈልግም ስማቸውንም ሙዚቃውንም አትነግሩኝም እዛው መድረክ ላይ እንገናኝ ነው ያልኳቸው፡፡ ይሄ ራሱ ትንግርት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ያ ነው እንግዲህ ድልድይ መሆኑን እዛ ጋ እንደምሳሌ ላሳይህ ነው፡፡ እዛው መድረክ ላይ እኔ የማላውቃቸውን ሙዚቃዎች ነው የማገኘው እኔም ኢትዮጵያዊነቴን ወይም እኔነቴን ይዤ እሄዳለሁ፤ የሚፈጠረውን አብረን እናያለን፡፡ ብቻዬን ከነሱ ጋ እጫወታለሁ ማለት ነው፡፡ ሙዚቃ ይሄ ነው፡፡ ጥበብ ፍቅር አንድ ነው ቋንቋው፡፡ እኔ ደግሞ የኖርኩበት ነው ይሄን ነገር፡፡ ‘ኢምፕሮቫይዝ’ በሚሉት ነገር ከማንኛውም ሙዚቀኛ ጋር ወዲያው እግባባለሁ፡፡
አል ዐይን ፡ ደስ ይላል! በእኔ በኩል ያሉትን ጥያቄዎች ጨርሻለሁ የምትለው ነገር ካለ እድሉን ልስጥህ?
መላኩ ፡ ሁላችንም ወደ ውስጣችን እንመልከት፤ ሌላው ላይ ከመፍረዳችን በፊት እኔ ምን ሰራሁ እንበል የየራሳችንን ድርሻ እንወጣ ብዬ አስባለሁ፡፡ ትንሽ ነው ብለን አናስብ የእኛን አስተዋጽዖ ነው፤ የእንባ ጥርቅም ነው ጎርፍ የሚሆነው፡፡ በተረፈ ፈንድቃ ባህል ማዕከል ልክ ከአሁን ቀደም ወረርሽኙ በመጣ ጊዜ እንዳደረግነው ሁሉ ስራዎቻችንን በቀጥታ ስርጭት በኦን ላይን በዩ ቲዩብ ወደ አድናቂዎቻችን እናደርሳለንና ጥበብንም ማገዝ ስለሆነ ‘ሰብስክራይብ’አድርጉን፡፡
አል ዐይን ፡ እናመሰግናለን፡፡
መላኩ ፡ እኔም አመሰግናለሁ፡፡