አዲሱ የአድማስ ድጅታል ሎተሪ ለአዟሪዎች ስጋት ይሆን…?
አስተዳደሩ በ 14 አይነት የሎተሪ እድል መሞከሪያ እጣዎች እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ በመሸለም ላይ ነው
የብሔራዊ ሎተሪ የአስተዳደር 10 ሺህ ሎተሪ አዟሪዎች አሉት
ከ60 ዓመት በፊት ስራ የጀመረው ብሔራዊ ሎተሪ የሎተሪ እድሎችን በቁጥር እና በሽልማት መጠን በየጊዜው እያሳደገ አሁንም ቀጥሏል።
አስተዳድሩ አሁን ላይ 14 አይነት የሎተሪ እድል መሞከሪያ እጣዎች ያሉት ሲሆን ቶምቦላ፣ ዝሆን፣ እንቁጣጣሽ፣ ትንሳኤ፣ የገና ስጦታ፣ ልዩ፣ ቢንጎ፣እና ፈጣን ዋነኞቹ ናቸው።
አሁን ላይ ተቋሙ ከ15 እስከ ሁለት ወራት የሚቆዩ የሎተሪ አሸናፊ እጣዎች ያሉት ሲሆን ለባለ እድለኞች እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ በመሸለም ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።
ብሔራዊ ሎተሪ ከሁለት ወራት በፊት ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ቦታ ሆነው የሞባይል ስልካቸውን ተጠቅመው ባለ እድለኛ የሚሆኑበት አድማስ ድጅታል ሎተሪ የሚል አዲስ አሰራር ዘርግቷል።
አል ዐይን አማርኛ ስለዚህ ጉዳይ ከተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ቴድሮስ ነዋይ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ይህ አሰራር በተለይም በወረቀት እየታተመ በሎተሪ አዟሪዎች አማካኝነት ለህዝቡ በሚሸጡ የሎተሪ ሽያጭ ሂደቶች ላይ እንከን አይፈጥርም? ሎተሪ በማዞር የሚተዳደሩ ዜጎችን ህይወትስ አይጎዳም? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን መልሰዋል።
ብሔራዊ ሎተሪ በሀገሪቱ ሁሉም ቦታዎች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ቋሚ ደንበኞች አሉት፣ ይህ አሰራር አይቋረጥም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አስተዳድሩ 10 ሺህ ሎተሪ አዟሪዎች አሉት የሚሉት አቶ ቴድሮስ አድማስ የተሰኘው የድጅታል ሎተሪ አሰራር የሎተሪ እጣ መግዛት ለማይችሉ ተደራሽ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ለመድረስ ሲባል መዘርጋቱንም ገልጸዋል።
አድማስ የድጅታል ሎተሪም ሆነ የወረቀቱ ሎተሪ በሚያስገኙት የሽልማት መጠን፣ እጣው በሚገዛበት ዋጋ እና አጠቃላይ አሰራራቸው እርስ በርሳቸው የማይተካኩ እንደሆኑም አቶ ቴድሮስ አክለዋል።
አድማስ የድጅታል ሎተሪ ዜጎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት ወደ 605 አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ አንድ የሎተሪ እጣ በሶስት ብር የሚገዙበት አሰራር ነው።
አዲሱ አሰራር ከተጀመረ ጊዜ አንስቶም ሁለት ጊዜ የአሸናፊ እጣ ቁጥሮች ይፋ የተደረጉ ሲሆን አንደኛ አሸናፊ እጣ ቁጥር 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያሸልማል።
ይሁንና አሰራሩ ገና አዲስ በመሆኑ እና ህብረተሰቡ የለመደው የወረቀቱን ሎተሪ በመሆኑ የታሰበውን ያህል ሰው እየተሳተፈበት ባለመሆኑ እየተገኘ ያለው ገቢም አነስተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
በቀጣይ የሚሳተፈው ሰው እየጨመረ ሲሄድ የሽልማት መጠኑም አብሮ ይጨምራል ብለዋል አቶ ቴድሮስ።
በአድማስ ድጅታል ሎተሪ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በትብብር የሚሰራ ሲሆን 25 በመቶው ለኢትዮ ቴሌኮም ቀሪው ደግሞ ለብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር ገቢ ይውላል ተብሏል።
የኦንላይን ሎተሪን መቼ ልትጀምሩ አስባችኋል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም የኢንተርኔት ወይም ኦንላይን ሎተሪ ብዙ መሰረተ ልማት እና ዝግጁነት ስለሚጠይቅ ይህን አሰራር በቅርቡ እንጀምራለን ብለን አናስብም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።