የ2022 የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ አሸናፊ ኢትዮጵያዊያን “ወደ አሜሪካ የመጓዝ እድላችን እየጠበበ ነው” አሉ
በድቪ 2022 ፕሮግራም ሶስት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን እድለኛ ሆነው ተመርጠው ነበር
የአሜሪካና ኢትዮጵያ ወቅታዊ ግንኙነት የድቪ እድለኞችን እየጎዳ መሆኑ እድለኞቹ ተናግረዋል
የ2022 የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ አሸናፊ ኢትዮጵያዊያን ወደ አሜሪካ የመጓዝ እድላቸው የጠበበ ነው ተባለ።
አሜሪካ በዓለም ላይ በየዓመቱ 50 ሺህ ሰዎችን በዳይቨርሲቲ ሎተሪ ወይም ድቪ አማካኝነት ወደ ሀገሯ ትወስዳለች።
ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ 38 ሺህ ሲሆን በድቪ 2022 ፕሮግራም 2 ሺህ 988 ኢትዮጵያውያን የእድሉ አሸናፊዎች ነበሩ።
እነዚህ ኢትዮጵያዊያን የድቪ ሎተሪ እድለኞች በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ካሳለፍነው ጥቅምት እስከ ያዝነው መስከረም ድረስ የቪዛ አገልግሎት አግኝተው ወደ አሜሪካ ምድር መሄድ አልያም በሂደት ላይ መሆን ነበረባቸው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የ2022 ኢትዮጵያዊያን የድቪ እድለኞች ለአል ዓይን እንዳሉት አዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ በተገቢው መንገድ እያስተናገደን አይደለም ብለዋል።
በአሜሪካ ድቪ ሎተሪ አሰራር መሰረት እድል እንደወጣልን ግንቦት ሰባት 2021ላይ አወቅን የሚሉት እነዚህ ግለሰቦች የቪዛ ፕሮሰሳችን እስከ መስከረም 30 ቀን 2022 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ማለቅ ቢኖርበትም እስካሁን ኢምባሲው አልጠራንም ብለዋል።
ኢምባሲው ከድቪ 2022 እድለኛ ከሆኑት 2 ሺህ 988 ኢትዮጵያውያን ውስጥ የቪዛ አገልግሎቱን የተጀመረላቸው ሰዎች ከ500 በታች እንደሆኑም እነዚህ እድለኞች ነግረውናል።
ከኢምባሲው የእስካሁኑ አገልግሎት ተነስተን በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የሆኑ ቀሪ የዲቪ 2022 እድለኞችን ያስተናግዳል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አክለዋል።
ኢምባሲው የቪዛ አገልግሎት እንዲጀምርልን ስንጠይቀውም በኮሮና ቫይረስ እና በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ጦርነት ምክንያት በርካታ የቪዛ አመልካቾች ስላሉ ጠብቁ ይለናል የሚሉት እነዚህ ድቪ የወጣላቸው እድለኞች ኢምባሲው የመተባበር ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል።
ከዚህ ይልቅ ግን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት እየተበላሸ መምጣቱ ለኢምባሲው የአገልግሎት መጓተት እና ፍላጎት ማጣት በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በሌላ ሀገራት ያሉ የአሜሪካ ኢምባሲዎች ከኢትዮጵያ የባሰ አስቸጋሪ ሁኔታ ያለባቸው ሀገራት ውስጥም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ለድቪ እድለኛ ሰዎች የቪዛ አገልግሎት እንደሚሰጡ እናውቃለንም ብለውናል።
ለአብነትም ከአንድ ዓመት በፊት ከራሷ አሜሪካ ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረው ታሊባን አፍጋኒስታንን ሲቆጣጠር የድቪ እድለኛ አፍጋኒስታዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተወስደው ቪዛ እንዲያገኙ እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
እኛ የ2022 ድቪ ሎተሪ የደረሰን ኢትዮጵያዊያን ግን አዲስ አበባ ባለው ኢምባሲ ማስተናገድ ካልቻላችሁ በጎረቤት ሀገራት ባሉ የአሜሪካ ኢምባሲዎች አስተናግዱን ብለን ብንጠይቅም የቪዛ አገልግሎት ጥያቄ ማቅረብ እንዳንችል ታግደናል ብለውናል።
በአሜሪካ የድቪ ሎተሪ እድለኞች አሰራር መሰረት የቪዛ ጥያቄ ማቅረብ እና አገልግሎቱን ማግኘት የሚቻለው እድሉ በተሰጣቸው ዓመት ውስጥ ከጥቅምት እስከ መስከረም ባሉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ መሆኑን ብናውቅም ችግሩ በእኛ በእድለኞቹ የተፈጠረ ባለመሆኑ ኢምባሲው ችግራችንን ሊያይልን ይገባል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኢምባሲ ለዓል አይን በሰጠው ምላሽ " የድቪ ሎተሪ እድለኛ ተሆነ ማለት ቪዛ ይገኛል፣ ለቪዛ ቃለመጠይቅ ይጠራል ወይም ቪዛ ይሰጣል ማለት አይደለም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ነገር ግን የድቪ ሎተሪ እድለኛ መሆን የቪዛ ጥያቄ ለማቅረብ የመጀመሪያው መስፈርት ነው ያለው ኢምባሲው እድለኞቹ አሁን ላይ የቪዛ አገልግሎት ሂደት ውስጥ ሳይገቡ ከቀረ በቀጣይ በሚደረጉ ተመሳሳይ የቪዛ አገልግሎት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ ሲልም ኢምባሲው ለዓል ዓይን በሰጠው ምላሽ አክሏል።
አሜሪካ በየዓመቱ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አውስትራሊያ 50 ሺህ ሰዎችን በድቪ ሎተሪ ወደ ሀገሯ ታስገባለች።
አፍሪካ የዚህ እድል ትልቁን ኮታ የምትሸፍን ሲሆን በድቪ 2022 ፕሮግራም ግብጽ፣ አልጀሪያ እና ሱዳን እያንዳንዳቸው ስድስት ሺህ ሰዎች እድለኞች ሲሆኑ ሞሮኮ 4 ሺህ 138 ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 3 ሺህ 347 ፣ጋና 3 ሺህ 145 ፣ኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺህ 988 ሰዎች የድቪ እድለኛ እንደሆነ ከተቋሙ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።