ብድር ለማግኘት የሞተ ሰው ወደ ባንክ የወሰደችው ብራዚላዊት ተያዘች
እንስቷ የአዛውንት አስከሬን በዊልቼር እየገፋች በመውሰድ ነው በስማቸው ብድር እንዲሰጣቸው የጠየቀችው
የ42 አመቷ ጎልማሳ አጎቴ ነው ያለችው አዛውንት ፈርመው ብድሩን እንዲወስዱ ብትጠይቃቸውም ትንፍሽ አለማለታቸው የባንክ ሰራተኞችን አጠራጥሯል
በላቲን አሜሪካዋ ሀገር ብራዚል ከሰሞኑ በባንክ እንግዳ ነገር ተከስቷል።
የ42 አመቷ ኢሪካ ቬይራ ኑኔስ በሪዮ ዴጄኔሮ ባንጉ በተባለ አካባቢ ወደሚገኝ ባንክ የ68 አመት አዛውንት በዊልቸር እየገፋች ታመራለች።
ፓውሎ ሮቤርቶ ብራጋ የተባሉት አዛውንት “አጎቴ ናቸው፤ ሞግዚያቸው ሆኘ የምንከባከባቸውም እኔ ነኝ” በማለትም ብድር ፈልገው እንደመጡ ለባንኩ ሰራተኞች ትናገራለች።
3 ሺህ 200 ዶላር ብድር ፈልገዋል የተባሉት አዛውንት ግን ዊልቼር ላይ ከመቀመጣቸው ባሻገር ትንፍሽ አላሉም።
ኑኔስ ጭንቅላታቸውን ደገፍ አድርጋቸው ማናገሯን ብትቀጥልም ምላሽ የለም።
“አጎቴ ትሰማኛለህ? መፈረም አለብህ፤ የማትፈርም ከሆነ ብድሩን መውሰድ አትችልም፤ ፈርም እንጂ፤ ራሴን አታሳምመኝ” ስትልም ከአዛውንቱ ምላሽ የለም።
የባንኩ ሰራተኞች በሁኔታው ግራ በመጋባት ስለጤንነታቸው ቢጠይቁም “ደህና ነው” የሚል ምላሽ መስጠቷን የብራዚል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
አጠቃላይ የአዛውንቱ ሁኔታ ያጠራጠራቸው የባንኩ ሰራተኞች ወዲያው ለአስቸኳይ ጊዜ ሰራተኞች እና ለፖሊስ መደወላቸውን ተከትሎ የ42 አመቷ ጎልማሳ አሳዛኝ ድርጊት ተጋልጧል።
እንስቷ በዊልቼር እየገፋች የወሰደቻቸው ፓውሎ ሮቤርቶ ብራጋ ህይወታቸው ማለፉ ይረጋገጣል።
አስከሬናቸውን ይዛ ባንክ ያመራችው ኑኔስ አምታትታም ቢሆን በሟቹ ስም ለመውሰድ በማሰብ መሆኑንም ፖሊስ ገልጿል።
ጠበቃዋ ግን ፖሊስ መረጃውን አዛብቶታል፤ አዛውንቱን ባንክ እስኪገቡ ድረስ ህይወታቸው አላለፈም በሚል አስተባብለዋል።
ፖሊስ ግን ኑኔስ አዛውንቱ አጎቴ ነው ማለቷ ሀሰት መሆኑንና ሞግዚት ነኝ በሚል ከባንክ ለማጨርበር ያደረገችው ሙከራም በወንጀል ያስጠይቃል ብሎ በቁጥጥር ስር አውሏታል።