ለልጁ ማሳደጊያ ላለመክፈል ሞቱን ያወጀው አሜሪካዊ እስርና የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል
የኬንታኪ ነዋሪው ሟቾች የሚመዘገቡበትን ስርአት ሰብሮ በመግባት ነው “ሞቻለሁ” ብሎ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሞከረው
ግለሰቡ ለቀድሞ ባለቤቱ 100 ሺህ ዶላር ላለመክፈል የዘየደው መላ ውስብስብ ችግር ውስጥ ከቶታል
የ39 አመቱ አሜሪካዊ ለልጁ ማሳደጊያ እንዲከፍል የተወሰነበትን ገንዘብ ከመስጠት ሞቱን ማወጅ መርጧል።
ጄሴ ኪፕ የተባለው የኬንታኪ ነዋሪ በካሊፎርኒያ ለምትኖር የቀድሞ ባለቤቱ 100 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል፤ ለልጁ ማሳደጊያ የሚሆን።
ለቀድሞ ባለቤቴ ድንቡሎ ሳንቲም ከምሰጥ ይልቅ “ሞቼ ልገላገል” በሚልም ህልፈቱን በራሱ ያውጃል።
ኪፕ የሃዋይ የሟቾች ምዝገባ ስርአትን ሰብሮ በመግባትም መሞቱን ያረጋግጣል።
ግለሰቡ መሞቱን የህክምና ባለሙያ በመረጃ ስርአቱ ውስጥ ገብቶ ማረጋገጥ ስለነበረበትም ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ በሃዋይ ከአንድ ዶክተር የይለፍ ቃልና ተያያዥ መረጃዎችን መስረቁ ተገልጿል።
ጄሴ ኪፕ የራሱን ስም፣ ዲጂታል ፊርማ እና የመታወቂያ ቁጥር በዶክተሩ አድራሻ አማካኝነት በማስገባቱም “መሞቱ” ተረጋግጦ በሁሉም የመንግስት ተቋማት “ሟች” ሆኖ ተመዝግቧል።
“ሟቹ” ኪፕ ግን ለልጁ ማሳደጊያ ላለመክፈል ሞቱን ካወጀ በኋላ እንደሞተ ሰው አርፎ አልተቀመጠም።
ስሙ ከመሬት በታች ስለተቀበረ በሀሰተኛ የማህበራዊ ደህንነት ቁጥር አዲስ ክሬዲት ካርድ ለማውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ስር ውሏል።
ኪፕ በሌሎች ሰዎች ስምና አድራሻ በአሪዞና እና ቬርሞንት ግዛቶች የሚተዳደሩ ድረገጾችን እንዲሁም የግል የንግድ ተቋማት የመገበያያ ስርአቶችን ሰብሮ በመግባት ያገኛቸውን የግለሰቦች መረጃዎች ለመሸጥ መሞከሩንም አልካደም ይላል የሚረር ዘገባ።
የበርካታ ሰዎችን የግል መረጃ የመነተፈው ኪፕ በቁጥጥር ሲውል በቤቱ ውስጥ በርካታ ኮምፒውተሮችና ስማርት ስልኮች ተገኝተዋል።
በሀሰት ሞቱን ያወጀውና በኮምፒውተር በሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች የተከሰሰው ግለሰቡ፥ ለቀድሞ ባለቤቱ 116 ሺህ ዶላር፤ የመረጃ ብርበራና ስርቆት ለፈጸመባቸው የመንግስትና የግል ተቋማት 79 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል።
ጀሴ ኪፕ በነገው እለትም በምስራቃዊ ኬንታኪ የወረዳ ፍርድቤት ሲቀርብ እስከ 7 አመት የሚደርስ እስራትና 500 ሺህ ዶላር ቅጣት ሊተላለፍበት እንደሚችል ተዘግቧል።