በ24 አመት ውስጥ 17 ጊዜ የወሊድ ፈቃድ የወሰደችው ጣሊያናዊት ተከሰስች
ትራስ በሆዷ ይዛ አረማመዷንም የነፍሰጡር በማስመሰል ለአመታት ቀጣሪዎቿን ስታጭበረብር የቆየችው የ50 አመቷ ጎልማሳ አንድም ልጅ አለመውለዷ ግርምት ፈጥሯል
ግለሰቧ በወሊድ ሰበብ ለአመታት ከስራ ከመቅረቷ ባሻገር ከ120 ሺህ ዶላር በላይ የወሊድ ድጎማ ወስዳለች ተብሏል
በጣሊያን እርግዣለሁ በሚል ከስራ መቅረትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን መውሰድን ተክናበት ቆይታለች የተባለችው እንስት በመጨረሻ ተደርሶብታል።
ባለፉት 24 አመታት ውስጥ በጥቂቱ 17 ጊዜ በሀሰት አርግዣለሁ እያለች ለአመታት ያለስራ የተከፈላትና ከ120 ሺህ ዶላር በላይ የወሊድ ድጎማ የወሰደችው የ50 አመት ጎልማሳ ባርባራ ሎሊ ትሰኛለች።
የጣሊያኑ ላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ እንደዘገበው ባርባራ ትራስ ሆዷ ውስጥ በማስቀመጥ ያረገዘች መመሰልና አረማመዷንም በነፍሰጡሮች ቅኝት የማድረግ ልምድን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አካብታለች።
ከአንድ ቢሮ ወደሌላ እየቀየረች “አርግዣለሁ የወሊድ ፈቃድ ይሰጠኝ” ስትልም ማንም አልተጠራጠራትም ይላል ዘገባው።
ባርባራ ከ17ቱ እርግዝናዎች 12ቱ ጽንሱ ተጨናግፎብኝ አልተሳካም፤ በአምስቱ ግን ቤኔዴትፋ፣ አንጀሊካ፣ አብራሞ፣ ሌቲዚያ እና ኢስማኢል የተባሉ ልጆች ወልጃለሁ ብትልም ልጆቿን ለማንም አሳይታ አታውቅም፤ የተመዘገቡበት ሰነድም የላትም።
ባለፈው አመት 5ኛ ልጄን ወለድኩ ስትል ለወላጆች የሚሰጥ የመንግስት ድጎማን የሚከታተሉ ፖሊሶች ማጣራት ሲጀምሩ ግን ባርባራ አለመውለዷንና አምስት ልጆች አሉኝ ያለችውም ቅጥፈት መሆኑን ደርሰውበታል ነው የተባለው።
ምንም የድህረ ወሊድ ክትትል ሳይደረግ ከ120 ሺህ ዶላር በላይ መውሰዷ የሚመለከታቸውን አካላት ትዝብት ውስጥ መጣሉን የዘገበው ላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ፥ ጎልማሳዋ ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ በተጭበረበሩ ሰነዶች 17 ጊዜ የወሊድ ፈቃድ መውሰዷን አመላክቷል።
ፈቃድ እና የወሊድ ድጎማ ገንዘብ ለመውሰድ እርግዝናዋን የሚያሳዩ ሀሰተኛ የሀኪሞች ፊርማ ያለባቸው እንዲሁም የልደት ማስረጃ ሰነዶችን ማቅረቧንም ነው የጣሊያን ፖሊስ ያስታወቀው።
የ55 አመቱ ባለቤቷ ዴቪድ ፒዚናቶም ተይዞ ምርመራ ሲደረግበት “ባለቤቴ ከ2012 ጀምሮ ነፍሰጡር እንዳልነበረች አውቃለሁ” ብሏል።
ቅጣቱ እንዲቀልለትም የትዳር አጋሩን የሀሰት እርግዝና የሚያጋልጡ ማስረጃዎችን ለፖሊስ ለመስጠት ቃል ገብቷል።
ለሁለት አስርት አመታት ቀጣሪዎቿን እና የጣሊያን መንግስትን ስታጭበረብር ቆይታለች የተባለችው ባርባራ ሎሊ፥ ከአምስቱ ልጆቿ አንዱን እንኳን ማቅረብ ባትችልም የገጠመኝን የጤና እክል ያሳያሉ ያለቻቸውን ሁለት ማስረጃዎች አቅርባለች።
የእነዚህ ማስረጃዎች ትክክለኝነትም አጠያያቂ ነው የተባለ ሲሆን፥ ከስራ ገበታ በመቅረት፣ የመንግስትን የወሊድ ድጎማ ያለአግባብ በመጠቅም፣ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት እና ሌሎች ክሶች የአመታት እስራት እና የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃት ተገልጿል።