ልዩልዩ
ለ15 ዓመታት የህክምና ፈቃድ ላይ ያለው ሰራተኛ በደመወዝ ጭማሪ መስሪያ ቤቱን ከሰሰ
የአይ.ቲ ባለሙያው በህክምና ፈቃድ ላይ እያለ 5 ሺህ 500 ዶላር ወርሃዊ ደመዝ ይከፈለዋል
ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ቢሮ ያልገባው ሰራተኛው የሚከፈለኝ ደመወዝ ኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ ነው ሲል ቅሬታ አቅርቧል
ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ላለፉት 15 ዓመታት የህክምና ፈቃድ ላይ ያለው ሰራተኛ የደመወዝ ጭማሪ አላደረገልኝም በሚል መስሪያ ቤቱን መክሰሱ ተሰምቷል።
ኢያን ክሊፎርድ የተባለው የአይ ቲ ባለሙያ በህክምና ፈቃድ ከስራ ውጪ የሆነ ሲሆን፤ የሚሰራበት አይ.ቢ.ኤም የተባለው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ግን በወር 5 ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር አሊያም በዓመት 67 ሺህ ዶላር ይከፍለዋል።
የአሜሪካው ግዙፉ አይ.ቢ.ኤም የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሰራተኛው በጤና እክል ምክንያ ወደ ስራ የማይመለስ ከሆኑ ጋር ተያይዞም የጡረታ እድሜው እስከሚደረስ አሊያም ህይወቱ እስኪያልፍ ድረስ ነው ደመወዙን የሚከፍለው።
ይሁንና ኢያን ክሊፎርድ የተባለው ሰራተኛ ኩባንያው
የሚከፍለኝ ደመወዝ ኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ ነው፤ የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግም አልተካተትኩም በሚል ኩባንያውን ፍርድ ቤት ማቆሙ ነው የተገለጸው።
ኢያን ክሊፎርድ አይ.ቢ.ኤም የቴክኖሎጂ ኩባንያ የአካል ጉዳነኞች ተጠቃሚነት ፕላን መሰረት የደመወዙ 75 በመቶ ማለትም በወር 5 ሺህ 500 ብር ገደማ አሊያም በዓመት 67 ሺህ ዶላር ሲከፈለው መቆየቱን ኩባያው አስታውቋል።
የፕላኑ ዋና አላማም በህመም አሊያም በአካል ጉዳት ምክንያት ስራ መስራት ያልቻሉ ሰራተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሆነም ነው ኩባንያው የገለጸው።
ይህን ሁሉ ዓመት ያለ ስራ ደመወዝ ሲከፍለው የነበረን ኩባንያ ፍርድ ቤት ያቆመው ኢያን ክሊፎርድ፤ አሁን ካለው ኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግልኝ ይገባል ሲል ተከራክሯል።
የፍድር ቤቱ ዳኛ ግን ጉዳዩን ኢያን ክሊፎርድ ካየበት ውጪ በተለየ መንገድ አይተውታል የተባለ ሲሆን፤ ኩባንያው ለሰራተኞች በዚህ መንገድ ደህንነት ማስጠበቁ የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል።
ይህንን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ ኢያን ክሊፎርድ በመስሪያ ቤቱ ላይ ያቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጓል የተባለ ሲሆን፤ ጉዳዩ ግን መነጋገሪያ እንደሆነ ቀጥሏል።