“ምጥ ላይ ነኝ’’ ያለች ሴትን ለማዋለድ ካረፈው አውሮፕላን የጠፉ 14 ሰዎች እየተፈለጉ ነው
ከሞሮኮ ወደ ቱርኳ ኢስታንቡል ሲጓዝ የነበረውን አውሮፕላን ጉዞ ስፔን ላይ የገታችው ሴት ግን ምጥ አጣደፈኝ ማለቷ የሀሰት ነው ተብሏል
የስፔን ፖሊስ በተቀነባበረ መልኩ ስፔን ለመቅረት ከሞከሩት 28 መንገደኞች ውስጥ 14ቱን መያዙን ገልጿል
ባለፈው ረቡዕ ከሞሮኮዋ ካዛብላንካ ወደ ቱርኳ የንግድ ከተማ ኢስታንቡል ሲበር የነበረውን አውሮፕላን ብዙም የማይደጋገም ሁነት ገጥሞታል።
ከመንገደኞቹ አንዷ “ምጥ አጣደፈኝ በፍጥነት አውሮፕላኑ አርፎ ልጄን መውለድ አለብኝ” የሚል ውትወታዋን በጩኸት ታግዛ ማቅረብን ተያያዘችው።
የአውሮፕላኑ የበረራ ሰራተኞችም በቅርብ ርቀት የሚገኝን የአውሮፕላን ማረፊያን ማሰሱን ገፉበት።
እናም የስፔኗ ባርሴሎና ኤል ፕራት አውሮፕላን ማረፊያ “ልትወልድ” የተቃረበችውን እንስት በፍጥነት አውርዶ ህክምና የምታገኝበትን ሁኔት ለማመቻቸት ወሰኑ።
አውሮፕላኑ በኤል ፕራት አውሮፕላን ማረፊያ ድንገተኛ ድጋፍ ጠይቆ እንደቆም ግን 28 ሰዎች ከአውሮፕላኑ ወርደው ለማምለጥ ሙከራ አደረጉ።
የስፔን ፖሊስም ግማሾቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ቢውልም 14ቱ መንገደኞች የገቡበት አልታወቀም።
አስገራሚው ነገር ግን መዳረሻውን ኢስታንቡል አድርጎ እየተጓዘ የነበረውን አውሮፕላን ስፔን ላይ የገታችው ሴት ምጥ አጣደፈኝ ማለቷ የሀሰት መሆኑ ነው።
የህክምና ባለሙያዎች በርግጥ እንስቷ ነፍሰጡር ናት፤ ነገር ግን እንኳን ምጥ ሊያጣድፋት ምንም የህመም ስሜት የላትም ብለዋል።
እናም የስፔን ፖሊስ ይህቺን ግለሰብ ከሀኪሞች ተቀብሎ በቁጥጥር ስር አውሏታል።
ጉዳዩንም የተቀነባበረ ስፔን ላይ አምልጦ የመቅረት ሙከራ ነው ብሎታል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት 14ቱ መንገደኞች መካከልም አምስቱ ወደ ኢስታንቡል በሚደረገው ጉዞ ለመቀጠል መስማማታቸውን ነው ስካይ ኒውስ የዘገበው።
ቀሪዎቹ 9 መንገደኞችም የማምለጥ ሙከራውን ከመራችው ነፍሰጡር ጋር በሌላ የፔጋሰስ አየርመንገድ አውሮፕላን ወደ መጡበት ይሸኛሉ ተብሏል።
የስፔን መንግስት የመንገደኞቹን ዜግነት ይፋ አላደረገም።
228 መንገደኞችን አሳፍሮ የነበረው ኤርባስ321 አውሮፕላን ከሶስት ስአት መጉላላት በኋላ ኢስታንቡል ደርሷል።
መሰል የመንገደኞች የማምለጥ ሙከራ ባለፈው አመትም በተመሳሳይ ከካዛብላንካ ወደ ኢስታንቡል በሚደረግ ጉዞ ላይ ተሞክሯል ነው የተባለው።
በስፔኗ የወደብ ከተማ ማሎርካ በ”ምጥ ላይ ነኝ” ማወናበጃ 24 ስዎች ለማምለጥ ሙከራ አድርገው 12ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የስካይ ኒውስ ዘገባ አውስቷል።