ከብሪታኒያ ወደ ሩዋንዳ መመለስ ያሰጋቸው ስደተኞች “እየጠፉ ነው” ተባለ
የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት “የብሪታኒያ መንግስት እቅድ ስደተኖችን የመንከባከብ ግዴታን የሚጥስ” ነው ሲሉ ነቅፈውታል
በብሪታኒያ 44 ሺ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞቸ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ
ከብሪታኒያ ወደ ሩዋንዳ መመለስ ያሰጋቸው ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ከየመጠሊያ ጣቢያዎችና ሆቴሎች በመጥፋት እየተደበቁ መሆናቸው የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት ገልጸዋል፡፡
የብሪታኒያ መንግስት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች ጉዳዮችን በሩዋንዳ ሆነው እንዲከታተሉ በሚል ከሩዋንዳ መንግስት ጋር የሚልዮን ዶላሮች ስምምነት መፈራረሙ የሚታወቅ ነው፡፡
በስምምነቱ መሰረት ፤ በርካታ ችግሮች አልፈውና ድንበር አሳብረው ብሪታኒያ የገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ለመሄድ የሚያስችላቸው የአውሮፕላን ትኬት ይሰጣቸዋልም ነው የተባለው፡፡
ይሁን እንጂ፤ ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ ጉዳይ ያሰጋቸው በርካታ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች አሁን ላይ ያረፉባቸውን ስፍራዎች ለቀው እየጠፉ መሆናቸው የብሪታኒያ ቀይ መስቀል እና የስደተኞች ካውንስል እየገለጹ ነው፡፡
ተቋማቱ የብሪታኒያ መንግስት እቅድ ስደተኖችን የመንከባከብ ግዴታን የሚጥስ ነው ሲሉም ነቅፈውታል፡፡
የብሪታኒያ ቀይ መስቀል ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይክ አደምሰን “እቅዱ ጥገኝነት የሚጠይቁ በርካታ ሰዎችን እንዳስጨነቀ እየሰማን ነው ፤ ስምምነቱ ብዙም ተቀባይነት እንደሌለው እየነገሩን ነው” ብሏል፡፡
ማይክ አደምሰን የሰዎች ስነ ልቦናዊ ደኅንነት ስሜት እየተሸረሸረ በመሆኑ ሰዎች በጣም ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ውስጥ ለመግባት እያሰቡ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም ሲሉም አክሏል፡፡
የብሪታኒያ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒሰቴር ማንኛውም ስደተኛ ራሱን እንዳይጎዳና ራሱን እንዳያጠፋ ለመከላከል የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
በብሪታኒያ 44 ሺ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞቸ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ብሪታኒያ በርካታ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኖች ከሚሰደድባቸው የአውሮፓ ሀገራት አንዷ ስትሆን ባለፈው ዓመት ብቻ 28ሺ 526 ስደተኞች አስተናግዳለቸው፡፡
ሩዋንዳ ፤ በብሪታኒያ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል እስከ 157 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ስምምነት ከአንድ ወር በፊት መፈረሟ ይታወሳል።
ስምምነቱ፤ ስደተኞች ከሩዋንዳዉያን ጋር ተቀላቅለው ለመኖር የሚያስችል ነው ተብሎለታል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሴንት ቢሩታ "ስምምነቱ የስደተኞችን ደህንነት እና ክብር የሚያስጠብቅ እንዲሁም የመኖር ፍላጎት ካላቸው በቋሚነት እንዲሰፍሩ መብት የሚሰጥ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።